ኧረ አልሆንልኝም አለ
ኧረ አልሆንልኝም አለ /መነባንብ/
ኧር አልሆንልኝም አለ መንፈሴ አልገዛም አለ
የጭንቅ አማላጅቱ አንድ ብትዪኝ ምን አለ?
ጸሎት ምህላ አቃተኝ መንፈሴ ለንሰሐ ሸፈተ???
መንጸፈደይን ወደቅኩኝ ነፍሴ በኃጢያት ሸፈተ
እምቢ አለኝ ፆም ጸሎት እምቢኝ አለኝ ንስሐ
ስጋ መንፈሴ ኮብልሎ እየዋኘ ከዓለም ውሃ
ኧረ አንድ በይኝ እመቤቴ ወለላይቱ ተማለጂኝ
ጨርሶ አለም ሳይነጥቀኝ ከወደኩበት አንሺኝ
ነጭ ነጠላ አጣፍቼ ከቤተ መቅደስ ስወጣ
መጽሐፍ ቅዱስ ዘርግቼ ለስብከት መድረክ ስወጣ
ልብሰ ተክህኖ ለብሼ ንፍቅ ገባሬ ሰናይ ስሆን
ጥቅስ በቃሌ ስደረድር ለዜማ ቅኔ ስቀኝ
አካሌ እዚህ ሆኖ መንፈሴ እየሸፈተ
ነፍሴን በኃጢአት ገንዞ ስጋዬ ነፍሴን ጎተተ
*
*
*
ኧረ አንድ በይኝ እመብርሃን ወለላይቱ ተማለጂኝ
ጨርሶ ዓለም ሳይነጥቀኝ ከወደኩበት አንሺኝ
ማለዳ ኪዳን አድርሼ ቅዳሴ ጸሎት ጨርሼ
ከቤተክርስቲያን ወጥቼ ወደ ስጋ ገብያ ተመልሼ
በኃጢአት ባህር ስዋኝ የግፍ ዳንኪራ ስረግጥ እውላለሁ
የልጅነት ፀጋዬን አውጥቼ ብኩርናዬን እሸጣለሁ
እዚህ መልአክ መስዬ ላዬ በቅድስና በርቶ
ውጪ ከክፋት ከፍቼ ኃጢአት በጽድቄ ተተክቶ
በሀሜት የሰው ስጋ ስበላ በወንድሜ ሸር ስሸርብ
ስዋሽ ስቀጥፍ ውዬ ስሰርቅ ሳሽሟጥጥ ስሳደብ
ነጠላ ስለብስ ግን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስገባ
ሰዓሊለነ ቅድስት ስል ያለ ንስሐ እንባ
የመውደቂያዬ ጉድጓድ ጥልቀቱ ወሰን ዳርቻ የለውም
እዝነ ህሊናዬ ለዓለም እንጂ ለጽድቅ ቦታ የለውም
መሃረነ ክርስቶስ እንዳልል ተዘከረነ ፈጣሪዬ
ኃጢአት በደሌ አፈነኝ በሀፍረት ነደደ ህሊናዬ
ምን ብዬ ልጥራው ጌታዬን ተዘከረነ ብዬ
ስለእኔ መገረፉን የመስቀሉን ፍቅር አቃልዬ
እንዴት ማረኝ ልበለው ስለ ስጋ ጣዕም ተቃጥዬ
ምን ብዬ ልጥራው ጌታዬን?
ዓይኔን ወደ ፀፍፀፈ ሰማይ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንበር
አንስቼ ማየት አቃተኝ ማረኝ ብዬ ለመናገር
ለሰው ጻድቅ መስዬ የኃጢአት ጎተራ ሆኛለሁ
እንዴት አባቴ ቀና ብዬ መንበረ ጸባኦትን አያለሁ
እባክሽን እናቴ ወለላይቱ ተማለጂኝ
እንደቃና ዘገሊላ ባዶ ማድጋዬን ሙዪልኝ
ከፊቱ እንዳላፍር ከአማኑኤል ጋር አስታርቂኝ
ለተጠማ ውሻ እንዳዘንሽ ለመጻተኛው እዘኚልኝ
አንቺ የትሁታን ትሁት ርህሪይተ ልብ እናቴ
ከልጅሽ ከኢየሱስ አማልጂኝ እዘኚ ለእኔም እመቤቴ
አንቺ ውዳሴሽ የነፍስ ስንቅ ስምሽ ከማር የጣፈጠ
በላኤ ሰብ በእፍኝ ውሃ በምልጃሽ ከሞት ያመለጠ
አንቺ መላእክት የሚጎበኙሽ የካህናት አለቆች ምስጋናቸው
በመወሰን የማይወሰን እሳተ መለኮትን የቻልሽው
አንቺ በገነት በተሰደደ ጊዜ ለአዳም ተስፋ የሆንሺው
ዛሬም ለእኔ ሁኚኝ ስለ ነፍሴ ተዋሺው
እንጂ እኔማ አልቻልኩም የልቤ ንጽህና ጠፍቷል
ለጸሎት እንኳን ስቆም ልቤ ለሁለት ተከፍሏል
*
*
*
ኧረ አልሆንልኝም አለ መንፈሴ አልገዛም አለ
የጭንቅ አማላጂቱ አንድ ብትዪኝ ምን አለ?
እምቢ አለኝ ፆም ጸሎት እምቢኝ አለኝ ንስሐ
ስጋ መንፈሴ ኮብልሎ እየዋኘ ከዓለም ውሃ
የልቤን መወላወል የነፍሴን ድካም አበርቺ
በአማላጅነትሽ ስር ነኝ እና ከልጅሽ አስታርቂኝ አንቺ
ለሰው አይን ባይገለጥም ሰውሬ የሰራሁት ኃጢአት
አምላክን አሳዝኖታል የምኖርበት ሕይወት
ይኸው የምናገረው አይሰምር የወረወረኩት አይመታ
ስጋዬ አልተቀደሰ ገበታዬ በረከት የለውም
ዕውቀት ምርምር አይዘልቀኝም ህሊናዬ ፍሬ አይቋጥር
ዝርው ሆኖብኝ ቀርቶ የነፍስ የስጋዬ ምስጢር
ይኸው የማወራው ለሰው አይጥም ፍቅር ከእኔ ቤት ርቋል
መቆም መቀመጤ አያምርም ሰው በስራዬ ይማረራል
የኃጢአት ምንዳዬ ይኸው የኃጢአት ደሞዜ ይኸው
ስቃዬ ውስጤን በልቶታል
ለአንድነት የተናገርኩት ዛሬም ጉባኤ ይበትናል
እና አዛኝቱ ታረቂኝ ከልጅሽ ከአማኑኤል አማልጂኝ
ከሰው የሸሸኩትን ኃጢአት ጨርሶ በልቶ ሳይውጠኝ
የበላዪ ሰብዕ እመቤት እባክሽን ተማለጂኝ
አንቺ ሕይወቴን ዳብሺው ነፍሴ ዕርፍት እንድታገኝ
*
*
*
ኧረ አልሆንልኝም አለ መንፈሴ አልገዛም አለ
የጭንቅ አማላጅቱ አንድ ብትዪኝ ምን አለ???
* / / *
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለ መስቀሉ ክቡር