ሰማዕትነት
+++ ሰማዕትነት ማለት +++
ዓላዊ ነገስታት ፥ በሰለጠኑበት
የዓለማዊነት እሳቤ ፥ በሚዎደስበት
እግዚአብሔርን መፍራት ፥ ፍፁም በሌለበት
አምልኮ ውዳሴ ፥ ለክብሩ መቀኘት
የመቀደስ ሃሳብ ፥ በጠወለገበት
አሁን በዚህ ሰዓት …
በጎልያዶች ዛቻ ፥ በፈርዖናዊያን ምክር
በመስቀሉ ዕንቅብ ተደፍቶ ፥ ጣዖት በአዋጅ ሲከበር
ክርስቶስን ያሉ ፥ ሲገፉ ፥ ሲገረፉ
አንገታቸው ሲቀላ ፥ ደምን ከሰውነታቸው ሲያጎርፉ
ታቦት ባህር ሲጣል
ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል
አሁን በዚህ ሰዓት…
ሰማዕትነት ማለት
ምስክርነት ነው ፥ በኑሮ የሚገልጡት
አንድም
በዓላዊያኑ በነገስታቱ ፊት…
እኔ ክርስቲያን ነኝ
ከክርስቶስ ፍቅር ፥ የለም የሚለየኝ
ብሎ መመስከርና ለክብሩ መቀኘት
አንገቴ ይበጠስ ከማዕተቤ በፊት
ስለ ስሙ ልኑር ስለ ስሙ ልሙት
አንድም
ዓላዊ ነገስታት ፥ የስሜት ሕዋሳት
በፍትዎት ማዕበል ፥ ነፍስን ሲያስጨንቋት
ለአይን አምሮትና ፥ ለልብ ክፉ ምኞት ፥ አልገዛም ማለት
በንጹሕ አኗኗር ፥ መመስከር በሕይዎት
አንድም
ጎልያድ በበዛበት በዚህ ክፉ ዘመን
ለወገን ስለ መድረስ ህዝብን ስለማዳን
ተግዳሮትን ስለማራቅ ፥ ለቤቱ ስለመቅናት
መጀገን መታጠቅ ፥ የራስን ወንጭፍ ማንሳት ፥ መሆን እንደ ዳዊት
አንድም
ሀሰት በበዛና ፥ ፍርድ በተገመደለበት
ደካማና ምስኪን አንገት በደፋበት ፥ አሁን በዚህ ሰዓት
ከተገፉትና ከእውነት ጎን መቆም
ሀሰትን መገሰፅ ፥ ሀሰትን መቃወም
ስለ እውነት ዋጋ መክፈል
ስለ እውነት መመስከር
አንድም
መስቀል ቀባሪነት ፥
ጣዖት አክባሪነት
እንዲህ በበዛበት
እውነት እንዲገለጥ ፥ ዓለም እንዲያከብረው
ሰማዕትነት ማለት ፥ እሌኒን መሆን ነው
ሰማዕትነት ማለት
ቆስጠንጢኖስነት
ዮሴፍ ጌትነት
መስከረም 2013 ዓ.ም