ሰላም ለእናንተ ይሁን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ዳግማዊ ትንሣኤ 

/ሰላም ለእናንተ ይሁን/ 

ክርስቶስ ተንሥዓ እሙታን ….በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን 

አሰሮ ለሰይጣን ….አግዐዞ ለአዳም 

ሰላም ….እም ይእዜሰ 

ኮነ….ፍሥሐ ወሰላም 

ዳግማዊ ትንሣኤ ማለት ምን ማለት ነው? ይኽንን ጥያቄ አስቀድሞ መመለስ ገና ወደ  ክርስትናው ለሚመጡ እና እንዲሁም የዕድገታቸው መጠን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስነብባቸው  ብዙ ወጣቶች «ዳግማዊ ትንሣኤ ማለት ምን ማለት ነው? እንደገና ተነሣ ማለት ነውን? »  ብለው ይጠይቃሉ። ዳግማዊ ማለት «ሁለተኛ» ተብሎ ስለሚተረጎም አንዳንድ ወጣቶች ምን  ማለት ነው ብለው ቢጠይቁ አለዓዋቂ አያስደርጋቸውም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዕለተ  ትንሣኤ ቀጥሎ ያሉትን ዕለታት ሥያሜ ስትሰጣቸው፦ 

ሰኞ ማዕዶት፦ ይኽውም ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት፤ ከዲያብሎስ  እስራት ተፈትተን ነፃ የወጣንበት ማለት ነው።  

ማክሰኞ ቶማስ፦ ይኸውም ቶማስ «የጌታን ትንሣኤ ካላየሁ አላምንም» በማለት  ከሐዋርያት ጋር የተነጋገረበትና ጌታም «ጣትህን ወደዚህ  አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤  ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን» ማለቱ ይታሰብበታል። 

ረቡዕ አልዓዛር፦ ይኸውም በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ ፲፩ ላይ እንደተጻፈው የማርታና የማርያም ወንድም የጌታ ወዳጅ ሞቶ በተቀበረ በአራተኛው ቀን ጌታችን እንዳሥነሣው የሚታሰብበት ነው።  አልዓዛር ግን ተመልሶ ሞትን እንደቀመሰ ልብ ይሏል። አማናዊው  ትንሣኤ የሙታን በኲር ሆኖ የተነሣው የጌታችን ትንሣኤ ነው። 

ሐሙስ የአዳም ሐሙስ፦ ይኸውም አዳም በበደለ ጊዜ ከገነት ሲባረር አምላካችን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል የገባለት ዕለት ይታሰብበታል። 

ዓርብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፦ ይኽውም ጌታችን ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ በሦስተኛው  ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ተብሎ የሚሰበክበትና እኛን ለማዳን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ መሆኑ ይሰበክበታል። 

ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት፦ ይኽውም የትንሣኤው ተቀዳሙ ምስክሮች የመጀመርያዎቹ  ሠላሣ-ስድስት ቅዱሳት አንስት ይታሰቡበታል።

እሑድ ዳግማዊ ትንሣኤ፦ ጌታችን ለሐዋርያት ከትንሣኤው በኋላ በዝግ ቤት ሳሉ  የተገለጠበት 

በዚች ሰንበት ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ በር ውስጥ ሳሉ ገብቶ፤ በመካከላቸውም ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎ ሲገለጥላቸው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም። ሐዋርያትም  ለቶማስ ጌታ መነሣቱንና በዝግ ቤት ሳሉም ከመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለእናንተ ይሁን»  እንዳላቸው ሲነግሩት «እናንተ መነሣቱን ዓይተናል ብላችሁ ስትሰብኩ እኔ ደግሞ መነሣቱን  ሰምቼአለሁ ብዬ ልመሰክር በመሆኑ እኔም እንደ እናንተ ካላየሁ አላምንም» ብሏቸዋል።  ጌታችንም ልብና ኩላሊትን መርምሮ የሚያውቅ በመሆኑ የቶማስን አለማመንና መጠራጠርን  ለእራሱ ለቶማስ ነግሮ ቅዱስ ቶማስ የትንሣኤው ብሥራት ተካፋይ እንዲሆን አድርጎታል።  ሙሉው የወንጌል ቃል እንዲህ ይላል፦ 

ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ኢየሱስም ዳግመኛ። ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው። ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ። ጌታን አይተነዋል አሉት። እርሱ ግን። የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ከዚያም በኋላ ቶማስን። ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው። ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም። ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው። ዮሐ ፳፥፲፱-፳፱ 

ቅዱስ ቶማስም የትንሣኤውን ነገር ተረድቶ «ጌታዬ አምላኬ» ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቶ  ያመነበት ጌታችንም ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ «ዳግም ትንሣኤ»  ተብሎ ይጠራል።  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!! 

አብርሃም ሰሎሞን