ማን እንዳንተ

ማን እንዳንተ

…..አንተ ስታስተምር …..

እንኳን ደቂቆቹ ሊቁም እንኳ ሳይቀር

ሊያውም በጨለማ ይመጣል ለመማር

…..አንተ ሐኪም ስትሆን…..

ታማሚህ ቀን ቆጥሮ መቼ ይመለሳል

ስለበሽተኛህ ሰንበት እንኳ ይሻራል

መድኃኒት የሌለው ድውይ ይፈወሳል

…..አንተማ ስትሰጥ…..

 የለብህም እና ስስት ንፉግነት

የተራበን ከርሀብ ደጋሹን ከውርደት

ትታደገዋለህ ላንተ አንዳች አያቅት

…..ማንእንዳንተ ትሁት…..

በፈጠርከው ፍጥረት ሄደህ የተጠመክ

 ደቀመዛሙርትን እግራቸውን ያጠብክ

ግብዝነት ይዞህ አትል ሰረገላ

ትጓዛለህ እንጂ በአህያ ውርንጭላ

…..አንተ ዳኛ ስትሆን…..

ውስጥን ሳትመረምር ፍርድ አትገመድልም

    ፍትህ አታዛባም ጉቦ አትቀበልም

ሐሰት ከፍ ብላ  እውነት ዝቅ አትልም

…..አንተማ ስታፈቅር…..

ላፈቀርከን ስትል እኛ ሳናፈቅርህ

ነፃ ልታወጣን ከአባት ቀኝ መጥተህ

እስከሞት መውደድን እንዲያ እያሳየኸን

ቅሉ አንዳች ሳይገባን አንተ አምላካችንን

ስቀለው እያልን ባንተ ላይ አስፈርደን

አንተ አዳኛችንን በቀራንዮ ሰቀልን

በደላችንን ግን በምህረት አልፈኸው

ነፃ አወጣኸን ሞትን ድል ነስተኸው

…..ማንይሆን እንዳንተ…..

አንተ ያደረከውን ለማድረግ የቻለ

በዓለም ፈተና ከቶ ያልታለለ

ስለራሱ ጥቅም ሌላውን ያልጣለ

ፍጥረቱን ለማዳን ዋጋ የከፈለ

ንገረኝ ጌታ ሆይ እንዳንተ ማን አለ?

********//////**********

ከሳሚ የእማዬ ልጅ ከኢትዮጵያ ቅድስት ሥላሴ