የዕለተ ሰንበት – የ3ተኛው እና የመጨረሻው ቀን ጉባኤ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ

22ተኛ ጉባኤ የ 3ተኛው እና የመጨረሻው ቀን ጉባኤ በዕለተ ሰንበት ከሰዓት በኃላ ተካሄደ

መርሃ ግብሩ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ በመልአከ ጥበባት አባ ገብርኤል “ከሁሉ ርስቴ ይህች ርስት ትባልጣለች ደሜን አፋስሼባታለሁና” በሚል ርዕስ ትምህርት ተሰጥቷል በመልአከ ሰላም ቀሲስ መስፍን (ዶ/ር) ሁለተኛ ዙር ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። የተወሰኑ በሀገር ቤት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በተደረገ ጥናት የቤተ ክርስቲያን ሀብት፣ ንብረት፣ ገንዘብ እንዴት እንደሚላክን እና ይህንን ብክነተ እንዴት ማስቀረት እንደሚቻል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያ ድረስ መደረግ ሳላለባቸው ጥንቃቄዎች እና የመከላከል ሥራ እንዴት መሠራት እንዳለበትም በጥናታቸው ጠቁመዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኘቱ 3 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም

1. አቡነ ኤዎስጣጤዎስ

2. አቡነ ቴዎፍሎስ

3. አቡነ ናትናኤል

በየተራ መልእክት አስተባልፈዋል በተለይም አቡነ ቴዎፍሎስ “ኢንኅድግ ማኅበረነ” (“ማኅበራችንን አንተውም”) ዕብ 10፥25 በሚል ርዕስ ሰፊ ትምህርት አስተምረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን በተለይም በቤተ ክርስቲያናችን የሚፈፀመው የቅርስ ዘረፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መሄዱ የሚታወቅ ነው። በዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳት ወደ ውጪ ሀገር ከወጡ በኃላ ለሽያጭ ይቀርባሉ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ዜና የሚያሳዝን ቢሆንም ለሽያጭ የቀረቡትን ደግሞ በተቻለ ወደ ሀገር ቤት መመለስ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ኃላፊነት ነው።

በቅርቡም ለገቢያ የቀረቡ 4 የብራና እንዲሁም አንድ ጥቅል የብራና መጽሐፍ አንድነት ጉባኤው አባላቱ በማስተባበር እና ከ9,000 ዶላር በመሰብሰብ መጻሕፍቶቹን በመግዛት ለብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ በኩል ወደ ኢይትዮጵያ እንዲላክ አስረክቧል።

በተጨማሪም በዚህ በያዝነው ዓመት በኦሞ ዞን ለሚገኙ እና በ 16 ዓይነት ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔር ለሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌል ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት የ፩ ወር ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል።

በማስከተል የአገልግሎት ዘመናቸውን በአጠናቀቁ አባላት ምትክ ምርጫ ተካሂዶ ለአዲስ የሥራ አመራር አባላት የአገልግሎት ዘመናቸው የተባረከ እንዲሆን ጸሎት ማርያም ተደጎላቸዋል።

በዚህ የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣ ሥነ ጽሑፎች፣ መንፈሳዊ ትውኔት እንዲሁም የቡድን ውይይቶች ተደጓዋል።

የ2014 ዓ.ም  22ተኛ ጉባኤን ያዘጋጀውን የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና የደብሩ ቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት እያመሰገን እግዚአብሔር በሰላም ቢያደርሰን የ2015 ዓ.ም 23ተኛው ጉባኤ በሲያትል ከተማ እንዲደረግ ተወስኖል ከምሽቱ 11:00 pm ሲሆን ጉባኤው በጸሎት ተዘግቷል።

ለመጀመር ያነቃቃን ለመፈፀም ያበቃን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን።

አሜን!!!