እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
“በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ” መዝ ፷፬፥፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ በማለት ልባዊ ምኞቱን ሲገልጽ በታላቅ ደስታ ነው።
በሰው ጥረት ሳይሆን አምላካችን በቸርነቱ እና በፍቅሩ የገባልንን ቃል ኪዳን በማሰብ ዘመናትን እያፈራረቀ ዛሬ ለደረስንባት ዕለት በሰላም በጤና ስላደረሰን ከምስጋና በቀር ምንም ማድረግ አይቻለንምና እንደ መላዕክቱ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብርህ ተሞልታለች”(ኢሳ ፮፥፫) ብለን ምስጋናችንን እናቀርባለን። አባታችን ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ለዘር እንተርፍ ዘንድ እርሱንና ቤተሰቦቹን ጠብቆ እንዲሁም ከፍጥረታቱ መካከል አምላካችን ዓለምን ሲፈጥር “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” እንዳለ በኖኅ ጊዜ በነበረው የውኃ ጥፋትም ወደ መርከቧ ወንድና ሴት እያደረገ አራዊትንና እንስሳትን እንዲሁም በሰማይ የሚበሩትን ሁሉ ለዘር ማትረፉ ይታወቃል። አባታችን ኖኅም የምስጋና መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር አቅርቦ ተቀባይነትን ስላገኘ በቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ የሚል ቃል ኪዳን ለሰው ልጆች ተሰጥትዋል፦
“እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ። ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም። በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም” (ዘፍ ፰፥፳፩-፳፪) ።
ይኽ ቃል ኪዳን ዛሬም ድረስ እየሠራ በአምላካችን ቸርነት ዘመናት እየተቀያየሩ አዲስ ዘመንን ለመቀበል በዋዜማው ላይ እንገኛለን። መጪው ዓመት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና ለቅድስት አገራችን ብሩህ እንዲሆንልን እየተመኘን አዲስ ዓመትን ለመቀበል ተቀብለንም በተግባር እንድንገልጽ በሚያስችለን ዘመን ተሻጋሪ በሆነውና በውብ ቃላት በተሰነደው መልዕክት ፦
“ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ አንድነትዋን አክብራና አስከብራ የቆየች ለውጭ ወራሪም አልመች ያለችው በሃይማኖትዋና በታሪክዋ እየተከላከለች ነው። ምንም እንኳን አገራችን ኢትዮጵያና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፉ ቢሆኑም በብዙ ትዕግሥትና በብርቱ ጸሎት የተቃጣውን ፈተና ሁሉ በእግዚአብሔር ኃይል በመመለስ እስከ ዛሬ ድረስ አኩሪ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በዚህም የተነሣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ወደ ቦታ ቢዘዋወርና ቢጓዝ በእራሱ ስም የሚጠራ፣ በእራሱ ትውፊትና ሃይማኖት የሚመራ ስለሆነ የበላይነት እንጂ የበታችኝነት አይሰማውም። ይኽች አገር ከክርስትና በፊትም ሆነ በክርስትና እድሜዋ በሥልጣኔና በነፃነት ይልቁንም ደግሞ በፊደልና በሥነ-ጽሑፍ ከጥንታውያን ግብፆችና ከግሪኮች ጋር የምትወዳደር ነች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተችው ስጦታዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ከእነዚህም ስጦታዎች መካከል፦
ሀ) ሙሉ ትምህርት ለ) ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ
ሐ) ሥነ-ጽሑፍ ከነጠባዩ ከነሙያው መ) ኪነ-ጥበብ በየዓይነቱ
ሠ- ሥነ-ጥበብ በየመልኩ ረ) ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ
ሰ) እምነት ከነፍልስፍናው ሸ) ነፃነት ከነክብሩ
ቀ) አንድነት ከነጀግንነቱ በ) አገር ከነድንበሩ፤ ከነፍቅሩ
ተ) ስም ከነምልክቱ/ከነትርጉሙ/።
አሁንም ቢሆን ትውልዱ ጀግንነትን፣ አገር ወዳድነትን፣ ለታሪክ፣ ለባህልና ለሃይማኖት ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ቤተ ክርስቲያን የበኩሏ ድርሻ አላት።”
(አባ ጎርጎርዮስ ሊቀ ጳጳስ)
መላው የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አባላት እና ይኽ ትምህርት የሚደርሰን ሁሉ አዲስ ዓመትን ለመቀበል በሚደረገው ቅድመ ዝግጅት የዘመን ስንቅ የሆነውን ከላይ የተጠቀሰውን የትምህርት መልዕክት በሚገባ አድምጠን ወደ ተግባር ለመለወጥ መነሣሣት ይኖርብናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦
“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” (፩ኛ ጴጥ ፬፥፫)
ብሎ እንዳስተማረ በአዲስ ዘመን አዲስ ልብ አስፈላጊ ነው። አሮጌ ልብ የተባለው ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ያልተዘጋጀ እና የተነገረውን ልብ ብሎ አድምጦ ቃሉን በውስጡ ለማሳደር ፈቃደኛ ያልሆነው ነው። አሮጌው ልብ እንደ ድንጋይ የጠጠረ እና እውነትን ለመቀበል ፍጹም ያልተዘጋጀ ነው። አምላካችን በነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል እንደተናገረ፦
“በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።” ሕዝቅኤል ፲፩፥፲፱-፳
በአዲስ ዓመት የድንጋዩን ልብ አውጥቶ የሥጋ የሆነውን ልብ ሊሰጠን የታመነ አምላክ አለና “አቤቱ፥ ንፁሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።” መዝ ፶፥፲ በማለት ለሚጸልይ ሰው እንደ ቃሉ ይደረግለታል። አምላካችን “ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” (ራእይ ፳፩፥፭) ብሎ እንደተናገረ እኛም በአዲስ ዓመት በአዲስ መነቃቃት ውስጥ ለመገኘት ቃል እንግባ። የሥጋ ሥራ የሆነውን መለያየትን አስወግደን በአንድነት እንቁም። ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረንን የመንፈስ ፍሬዎችን ገንዘባችን እናድርግ፤ የሥጋ የሆነውን ሥራ ከእኛ እናርቅ። በመንፈስ እንጂ በሥጋ አንመላለስ። “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ገላ ፭፥፲፮-፳፫
ለአዲስ ዓመት በአዲስ መነቃቃት መጀመር መንፈሳዊነት ነው። እኛም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን “በሥጋ ምኞት የተመላለስንበት ያለፈው ዘመን ይብቃ” ብለን ከልባችን ወደ እምነታችን እንመለስ። ነቢዩ ሆሴዕ ዛሬም እንዲህ እያለ ይጣራልና እንስማው፦ “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል።” ሆሴዕ ፮፥፩ በመጨረሻም ዓመታትን በቸርነቱ የሚያቀዳጅ ልዑል እግዚአብሔር ከኃጢአት በስተቀር የተመኘነውን ሁሉ ይፈጽምልን።
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ በረከት አይለየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ከሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ
ቀን፦ ጳጉሜን ፬/፳፻፲፬ ዓ/ም