ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ

ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ

በዚህ ትምህርት ላይ መነሻ ርእስ አድርገን የምንማረው በወርኻ ታኅሣሥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው የአምላካችን፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል ያሉትን የሦስት ተከታታይ ሳምንታት በዓላት የሆኑትን ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው የተሠየሙትን ነው። እነዚህ ሦስት በዓላት ከታኅሣሥ ፯ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፯ ድረስ ባሉት ሦስት ሳምንታት የሚከበሩ ናቸው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለእያንዳንዱ ሳምንት እንደ ሥያሜያቸው ትምህርት አዘጋጅታ ልጆቿን ታስተምራለች፤ በዓላቱም በመዝሙር እና ጸሎት ሥርዓት ይከበራሉ። አስቀድሞ በነቢያት ሲነገር የነበረው እና ነቢያቱ አምልተውና አስፍተው የወልደ እግዚአብሔርን ሰው የመሆን ምሥጢር ማስተማራቸው፤ አምላካችን የጠፋውን ዓለም ለማዳንና የወደቀውን አዳምን ለማንሣት የሚያደርገውን ጉዞ በተስፋ ይጠባበቁ ለነበሩ ሁሉ መልካም ዜና የተሰማበትና የምሥራቹ ቃል የደረሰበት በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስተምህሮ ዘመነ ስብከት ተብሎ ይታወቃል። እነዚህ የየሳምንቱ ሥያሜዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ፦

፩ኛ ሳምንት) ስብከት

ስብከት ማለት ትምህርት ማለት ነው። ነቢያት የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆንና ድንግል በድንግልና ፀንሳ ጌታን እንደምትወልድ ምሥጢር ተገልጦላቸው በተስፋ ይጠባበቁ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ነቢዩ ኢሳይያስ «ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ» (ኢሳ ፷፬፥፩) በማለት ይጣራ የነበረው ይኽ ዓለም ለመዳን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያስፈልገው በማወቁ ነው። ከዚህ መልዕክት ጋር ተስማሚ ሆነው የቀረቡ ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይገኛሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተገልጦ ወደ ምድር እንደሚመጣ ከተነገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል እንዲህ ይላሉ፦

እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ (መዝ ፻፵፫ ፥፯)።

ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች (ኢሳ ፯፥፲፬)።

አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል (ሚክ ፭፥፪)።

«አቤቱ እጅህን ከሰማያት ልከህ አድነን» መዝ. ፻፵፫፥፲፯) ።

የጌታ ሐዋርያትም በሐዲስ ኪዳን ይኽንን የትንቢት ቃል ያውቁ ስለነበር ጌታችን ከእመቤታችን ተወልዶ ወደ ምድር ሲመጣ ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ እስራኤላውያንም «መሲሁን አገኘነው፤ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» በማለት አምነው ተከትለውታል (ዮሐ ፩፥፵፩ እና ፵፭) ። የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ አግኝቷልና ሐዋርያት በየትኛውም ቦታ በትምህርታቸው የነቢያትን ቃል እየተናገሩ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፦

ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን (ዕብ ፩፥፩-፪)

አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው (ሐዋ ፫፥፲፯-፲፰)።

በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ። በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም። የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ (፪ጴጥ ፫፥፩-፬)።

፪ኛ ሳምንት)ብርሃን

በዚህ በሁለተኛው ሳምንት ነቢያት በተስፋ ይጠባበቁት የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ከጨለማ ወደ ብርሃን ስለማምጣቱ፤ ወድቆ የነበረውና በዲያብሎስ እስራት ተይዞ የነበረው ሕዝብ ወደሚያስደንቅ ብርሃን የመምጣቱ ነገር ይሰበካል። ምክንያቱም ዓለም ብርሃን ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃል የራቀበት እና በድቅድቅ ጨለማ ራሱን የጣለበት ዘመን አልቆ ወደቀደመው ክብሩ የመመለሱ ነገር የሚሰበክበት ነው። ነቢያቱም “ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ” (መዝ ፵፪፥፫) እያሉ ይማጸኑ ነበር። በዚህ ዕለት አማናዊው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳችንን ነጥቆ ከሲዖል ጨለማ እንዳወጣንና እንዳዳነን በሰፊው ይሰበካል። ከእግዚአብሔር ተልኮ ሰዎችን ወደ ንስሐ የመለሰው ቅዱስ ዮሐንስ እውነተኛው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መምጣቱን እንዲህ ሲል ነገረን፦

ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም (ዮሐ ፩፣፱-፲፫) ።

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል (ዮሐ ፫፥፲፮-፳፩) ።

ዓለም በብርሃን ይመላለስ ዘንድ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ሕይወት ሰጥቶናልና ዳግም ወደ ጨለማ ሕይወት እንዳንጓዝ ራሳችንን መጠበቅ ይገባናል። ጌታችንም ሐዋርያት በዓለም እንዲያበሩ «እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ» ብሏቸዋል። እርሱም የዓለም ብርሃን ነውና አማናዊ ብርሃንነቱን ሲገልጽልን «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው (ዮሐ ፰፥፲፪) ብሎ ለሐዋርያት መንገሩ በሙላት ይሰበካል።

፫ኛ ሳምንት) ኖላዊ

የዚህ የሦስተኛው ሳምንት ስም «ኖላዊ» ይባላል። ኖላዊ ማለትም ጠባቂ እረኛ ማለት ነው። ነቢያት እረኛ እንዳጣ ከብት የተበተነውን ሕዝብ በማሰብ እውነተኛ የሆነው እረኝነትን በመጠባበቅ ይናገሩት የነበረው ትንቢት ይሰበክበታል፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ፦

«ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ። በኤፍሬምና በብንያም በምናሴም፤ ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና። አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን (መዝ ፸፱፥፩-፫)

በማለት ጠባቂ ለሆነው ለአምላካችን ዝማሬ ሲያቀርብ እንሰማዋለን። ከዚህ ጋር በተያያዘም እረኞች የተሰማሩበትን ቦታ ትተው በጎቻቸውን ለንጥቂያ ማድረጋቸውም ይነገራል። ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ እንዳለ፦

እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? … የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም … ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ … እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና፤ ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ።

ይኽ በነቢያት የተነገረው ቃል ፍጻሜ ያገኘው ጌታችን ለሁላችን እረኛ በመሆን በዮሐንስ ወንጌል ላይ የእርሱን እረኝነት እና የእኛን ጠባቂ የሚያስፈልገን በጎች መሆናችንን እንዲህ ባለ ቃል አስረድቶናል፦

መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። (ዮሐ ፲፥፲፩-፲፮) ።

በጥቅሉ በእነዚህ የሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ስብከት፤ ብርሃን፤ ኖላዊ በማለት ስለ አምላካችን፣ ጌታችንን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይነገራል። ከዚህ የነቢታ ጾም በረከት ተሳትፈን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም ያድርሰን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አብርሃም ሰሎሞን
የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ትምህርት ክፍል