የጌታችን መወለድና የልደት ዘመኑ

የጌታችን መወለድና የልደት ዘመኑ

ሰብዓ ሰገልም…ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ማቴ ፪፥፲-፲፩ 

እንኳን ለአምላካችን፣ ለጌታችን እና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሰን እያልን ስለ ጌታችን መወለድና ስለ ልደት ዘመን እንማማራለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህን እጅግ አስገራሚ የሆነ የአምላክን ሰው መሆን ሲያስተምር «ከዚህ የበለጠ ምሥጢር የለም»  ብሎ ይጀምራል። በሚያስደንቅ ጥበብ ነቢያት ከጻፉት አንዱም ሳይጎድል ሁሉም ነገር የተከናወነበት የልደት ምሥጢር ጌታችን ሲወለድ እንደተጻፈው ሆኖ ተፈጸመ። ልደቱ እኛን ነፃ ሲያወጣን ዲያብሎስን ግን አስራደው። በእባብ ተመስሎ አዳምንና ሔዋንን ያሳተው ከሳሽ ዲያብሎስ በሰው ተመስሎ ይኸውም በሔሮድስ ላይ አድሮ ሕፃናትን አስፈጀ። ፈርዖን «ወንዶች ልጆች ሲወለዱ የግብፃውያን አዋላጆች አንቀው ይግደሏቸው» ብሎ አዋጅ እንዳሳወጀ ሐሮድስም በዘመኑ ጌታን የሚያገኝ መስሎት «ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ ሕፃናት ይገደሉ» ሲል አዋጅ አስነገረ፤ አስነግሮም አስፈጃቸው። ሊያድነን የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ግን የዲያብሎስ ሥራ ሊይዘውና ሊያስቀረው አልተቻለውም። የጌታችንን የልደት በዓል ስናከብር፦ 

ከእመቤታችን ተወለደ፤ 

እውነተኛ ብርሃን ሆኖ መጣልን፤ 

ከዳግም ሞት አዳነን፤ ወ.ዘ.ተ. 

እያልን ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ ሄደን ፍጥረት እንዴት እንደሳተ እና ለጥፋታችንም ምክንያት የሆኑት እነማን ናቸው? ብለን በመጠየቅም ነው። ይኽንን ካላደረግን የመዳናችንን ነገር ለሌሎች ለማስረዳት እንቸገራለን። እስራኤላውያን ወደ ቅድስት አገራቸው መመለሳቸውን ስንናገር የግብፅን የባርነት አገዛዝ እንደምናነሣው ሁሉ በጌታችን ልደትም ነፃነታችን እንደታወጀልን ስንናገር ከአዳም ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ድረስ ያለውን ዘመን እያነሣን የዲያብሎስ ሥራ እንዴት እንደወደቀም በማስረዳት መሆን አለበት። 

ዘመነ ልደት 

ዘመነ ልደት የሚባለው ከታኅሣሥ ፳፱ ቀን ጀምሮ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ዘመነ ልደት መባሉም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነስቶ በመወለዱ ነው። በዚህ ጉዜም የጌታችን መወለድና የዓለማችን ድኅነት ማግኘት ይሰበካል። 

ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፣ ተገለጠ፤ 

የነቢያት ትንቢትም ቀድመው እንደተጻፉት ተፈጸመ፦ 

«የመውጊያውን ብረት ብታቃወም በአንተ ይብሳል» የተባለው፤ እንዲሁም አሥራ-አራት መልዕክታትን የጻፈው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ።» (ገላ ፬፥፬) ብሎ እንደተናገረ፤ የጌታችን የመወለድ ትንቢት በዐበይት እና በደቂቀ ነብያት የተሰበከው በዚህ በልደት ዘመን በሙላትና በስፋት ይነገርበታል። ምክንያቱም እውነተኛው የዓለም ብርሃን ከጨለማ ሕይወት አውጥቶ ዓለምን ወደቀደመ ክብሩ መልሶታልና። ስለሆነም ነቢያትን ያናገራቸው ርሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመምጣቱ ጉዳይ ነቢያት የተናገሩትን በማጣቀስ ትምህርት ይሰጥበታል፦ 

በነቢያት እንዲህ ተብሎ ነበር፦ 

በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። ዘፍ ፫፥፲፭ 

አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥ ዘኁ ፳፬፥፲፯ 

እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ኢሳ ፯፥፲፬ 

ሕፃን ተወልዶልናል፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳ ፱፥፮-፯ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። ሚክ ፭፥፪ 

የነቢያት ቃል ልደቱን በተመለከተ በምን መልኩ ፍጻሜ አገኘ? 

አምላካችን በቤተልሔም ተወለደ። (ማቴ. ፪፥፭-፮) 

አምላካችን ከድንግል ማርያም ተወለደ። (ሉቃ. ፪፥፯) 

ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተገለጠ፤ ለምንስ ወደ ምድር መጣ? 

፩) የሰይጣን ዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ፦ 

የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። (፩ ዮሐ ፫÷፰) ፪) የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን፦ 

የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷል። (ሉቃ. ፲፱፥፲) 

፫) ሕይወት ሊሆነን፦ 

እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። (ዮሐ. ፲፥፲) 

፬) ሰይጣን ዲያብሎስን ከሥልጣኑ ሊሽር። 

እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን  ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ  ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና  በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን  አይደለም። (ዕብ. ፪፥፲፬-፲፰) 

፭) ኃጢአተኞችን ሊያድን 

ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል  

የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ።  

(፩ጢሞ. ፩፥፲፭) 

፮) ስለ እውነት ሊመሰክር 

እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም  

መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል) ። (ዮሐ. ፲፰፥፴፯) 

፯) ዘላለማዊ ሕይወትን ሊሰጠን… 

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ  እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።  ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ  ዓለም አልላከውምና። (ዮሐ. ፫፥፲፮-፲፯) 

፰) ከኩነኔ ሊያወጣን 

እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ  ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት  አውጥቶኛልና። (ሮሜ. ፰፥፩-፪)

ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ሆኖ በምንስ ተመስሎ ሊያድነን ተገለጠ? 

 ፩) በእንጀራ ተመስሎ «የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።» ብሎ ፪) በብርሃን ተመስሎ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።» ብሎ 

፫) በበረት ተመስሎ «እኔ የበጎች በር ነኝ።» ብሎ 

፬) በእረኛ ተመስሎ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ።» ብሎ 

፭) በሕይወት ተመስሎ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ።» ብሎ 

፮) በመንገድ በእውነት በሕይወት ተመስሎ «መንገድም እውነትም ሕይወትም እኔ ነኝ።» ብሎ፣ 

፯) በወይን ተመስሎ «እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ።» ብሎ 

ከዚህ በተጨማሪም ሰው ሆኖ መጥቶልናል። ይኽንንም ሁኔታ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምርና ሲያስረዳ በዕብራውያን መልዕክቱ፦ 

«ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል  ሊቀ ካህናት የለንም።» (ዕብ. ፬፥፲፭) በማለት «እንደ እኛ» ሲል ሰው ሆኖ መምጣቱን በተገቢው መልክ ገልጾልናል። 

በአጠቃላይ በዚህ በልደት ዘመን ከላይ ያለው ትምህርት እና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸው ትምህርቶች በሰፊው ይሰጡበታል። 

ከአምላካችን፣ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በረከትና ራድኤት አምላካችን ያድለን። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

አብርሃም ሰሎሞን (ጸሓፌ ጥበብ) 

በሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ትምህርት ክፍል

Click here to download the PDF file