ቅድስት

የዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት ˝ ቅድስት ˝ ይባላል።

በምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤ/ክ

ሰ/ት/ቤ/ት ትምህርት ክፍል – ቨርጂኒያ /የካቲት 2010 ዓ.ም/

   የቅድስት መዝሙር

ግነዩ ለእግዚአብሔር

ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ

ለአሕዛብ ምግባሮ᎐᎐᎐

እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፤

ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሩ።

 የቅድስት ምስባክ

− እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፣

አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ።   

ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ።

እግዚአብሔር ሰማያትን ሠራ፣

ምስጋና ውበት በፊቱ ነው፣

ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።

 የቅድስት የቅዳሴ ምንባብ

1ኛ ተሰ᎐ 4፥1−13

−1ኛ ጴጥ᎐1፥13− እስከ ፍጻሜ ምዕራፍ

− ግ᎐ሐዋ᎐10፥17−30 የቅድስት ወንጌል

−ወንጌል ዘማቴዎስ 6፥16−25

የቅድስት ቅዳሴ

−ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ/ዐቢይ/

 

ቅድስት የተባለበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው። ስያሜውም የቅዱስ ያሬድ ሲሆን ፤ ቃሉ ግን የወጣው ወይም የተገኘው ˝ቀደሰ˝ አመሰገነ፣ ለየ፣ መረጠ፣ አከበረ ከሚለው የግዕዝ ግስ ነው። ስለዚህ ˝ቅድስት˝ የሚለው ቃል የሚቀጸለው ለሰንበት በመሆኑ ይህች ዕለትና ከዚህች ዕለት ተነሥተን የምንቆጥራቸው ሰባት ዕለታት ወይም አንድ ሳምንት ˝ ቅድስት ˝ ተብሎ ይጠራል።

ቅድስት ሰንበት የተለየች፣ የተከበረች፣ የተመረጠችና የተቀደሰች ናት። ቃሉ የተገኘበትን ግንድ (ቀደሰ) የሚለውን ቃል ስንመለከት ሰንበትን የቀደሰ እግዚአብሔርን እናገኛለን። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ በዚህም ምክንየት ከእግዚአብሔር ጋር የተያያዙ፣ ወይም ለእግዚአብሔር ክብር የተለዩ ሕዝቦች፣ ነገሮች፣ ዕቃዎች፣ ቦታዎችና ድርጊቶች የተቀደሱ ይሆናሉ። ለምሳሌ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ሲያዝዛቸው “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” ብሏቸዋል/ ዘሌ᎐ 19፥2/። ይህንንም ያለው እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ የተለዩ የራሱ ሕዝብ አድርጓቸው ስለነበር ነው። እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ለአምልኮታዊ አገልግሎት የምንጠቀምባቸው ዕቃዎች ሁሉ ንዋያተ ቅድሳት ይባለሉ። በተጨማሪም ሙሴና ኢያሱ እግዚአብሔርን ያነጋገሩባቸው ቦታዎች የተቀደሱ ስለሆኑ ጫማዎቻቸውን እንዲያወልቁ ታዝዘዋል።( ዘጸ᎐3፥5, 13፥2, 28፥41 ኢሳ᎐5፥15, 6፥3) … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

 እንኳን ለዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ!       

በሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ

የፍኖተ ሕይወት ሰ/ት/ቤት ትምህርት ክፍል – ቨርጂንያ

ስለ ዐቢይ ጾም መጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ) ከማንሣታችን አስቀድመን ጥቂት ስለ ጾም እና መንፈሳዊ ሥርዓቱ እናወሳለን።

  • Tseme Diguaጾም ማለት ለዘለዓለም ሁሉንም ሕዋሳት ከኃጢአት መከልከል፣ ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ እህል ከመብላት እና ውሃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከጥሉላት፣ ከሥጋ፣ ከወተት በአጠቃላይ ከእንስሳት ተዋጽኦ መከልከል ነው።  
  • ጾም የሥጋ ምኞትን የምታጠፋ፣ የነፍስን ቁስል የምታደርቅ፣ ለጎልማሶችም ጸጥታን እና እርጋታን የምታስተምር፣ ከእንስሳዊ ግብር ጠባይ የምትከለክል እና ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ደገኛ ሥርዓት ነች። 
  • ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓመቱ ውስጥ ምእመናን መንፈሳዊ በረከትን እንዲያገኙ የተለያዩ አጽዋማትን ሥርዓት አድርጋ ሠርታልናለች። ከነዚህ አጽዋማት አንዱ እና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው።

ዐቢይ ጾም

ይህ የጾም ወራት《ዐቢይ》 መባሉ ከአጽዋማት ሁሉ የላቀ መሆኑን ለማሳየት ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጾም ሳይገባው ለእኛ አርዓያ እና ምሳሌ ለመሆን በገዳመ ቆሮንቶስ የጾመው እና ዲያቢሎስን ድል የነሣበት በመሆኑ ነው። በሌላም መልኩ《ሁዳዴ》በመባል ይታወቃል። 《ሁዳድ》በሚለው ጥንታዊ ሰፊ የእርሻ መሬት ስም ታላቅነቱን ለመግለጽ ነው።

በዚህ የጾም ወራት በቤተ ክርስቲያናችን ጾመ ድጓ (ጾመ ምዕራፍ) ይቆማል፣ ዳዊት ይነበባል፣ ሥርዓተ ማኅሌቱ በመቋሚያ (በዝማሜ) ብቻ ይከናወናል። ወቅቱ የሱባዔ በመሆኑ በከበሮ እና በጸናጽል ሥርዓተ አምልኮ አይከናወንም። ዘወትር ስብሐተ ነግህ ይደርሳል። በሕማማት ሳምንት ደግሞ ትምህርተ ኅቡአት፣ ኪዳን ይተረጎማል፣ ትምህርተ ወንጌል ይሰጣል፣ ይጾማል ይሰገዳል፤ በሁለንተና ጌታ ይመለካል። 

በጾሙም እንደ መድኃኒታችን ጠላትን ድል እንነሣበታለን። የጾሙ አቆጣጠርም በ《ኢየዐርግ》እና《ኢይወርድ》 የሚገደብ ሲሆን ሲወርድ ከየካቲት ፪ ቀን ፣ ሲወጣም ከመጋቢት ፮ ቀን  ጀምሮ እስከ በዓለ ትንሣኤ ዋዜማ ያለው ፶፭ ቀን ዐቢይ ጾም በመባል ይታወቃል።

በዐቢይ ጾም ውስጥ ፰ ሰንበታት ሲኖሩ ቅደም ተከተላቸውም እንደሚከተለው ነው፥

ዘወረደ                     ደብረ ዘይት

ቅድስት                    ገብርኄር

ምኩራብ                   ኒቆዲሞስ እና

መፃጉዕ                     ሆሳዕና ናቸው።

ዘወረደ

ዘወረደ ማለት《 የወረደ 》ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት፣ የሰው ፍቅር አገብሮት ከሰማያት መውረዱን፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን፣ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከድንግሊቱ ተወልዶ በሥጋ መገለጡን (ዘፍ ፫፥፲፭ ፤ ፩ኛ ዮሐ ፫፥፰) የምናወሳበት ሳምንት ሲሆን በአጠቃላይ ዘወረደ ዕርቀ አዳም፣ ተስፋ አበው፣ ትንቢተ ነብያት ፣ ሱባዔ ካህናት የተፈጸመበት ፣ ኪዳነ አዳም መሲህ ክርስቶስ መወለዱን (በሥጋ መገለጡን) የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው። ስያሜውም የተወሰደው በዕለቱ ከሚዘመርው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ነው። … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Flyer_Regis_18_1

ወደ አብነት ትምህርት ገጽ ለመሄድ እዚህ ያጫኑ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!!!

“ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል።” (ማር፲፮፥፲፮)

“አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ኤፌ ፬፥፭

TimketFlyer2010የጥምቀት በዓል ሥነ-ሥርዓትና ምሳሌዎች

ጥምቀት ቃሉ የግዕዝ ሲሆን አጥመቀ ከሚለው ግሥ የተገኘ ነው። ትርጉሙም በገቢር መንከር፣መድፈቅ መዝፈቅ በተገብሮ ሲሆን ደግሞ መነከር፣መደፈቅ፣ መዘፈቅ፣ መላ አካልን በውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው።

የጥምቀት በዓል ዋዜማው “ከተራ” በመባል ይታወቃል። ከተራ ማለት መገደብ ማለት ነው። ታቦታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው በወንዝ ዳር ወይም በሰው ሰራሽ የውሃ ግድብ ዳር በዳስ/በድንኳን ውስጥ ያድራሉ።

የጥምቀት በዓል መነሻው የጌታችን የመድኃኔታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ነው። ጌታችን የተጠመቀው ለአዳምና ሔዋን ድኅነት ሲል ነው።

አዳምና ሔዋንን ሰይጣን በእባብ አማካይነት አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በስሕተት እንዲበሉ አድርጎ፣ ዕፀ በለስን በመብላታቸው ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነመ እሳት ተፈርዶባቸው ሳለ ዲያቢሎስ የአባታችን አዳምና የእናታችን ሔዋንን የእዳ ደብዳቤ አዳምና ሔዋን የዳቢሎስ ተገዢና አገልጋይ ብሎ ጽፎ በዮርዳኖስ ባሕርና በሲኦል ሸሽጎት ነበር። ለጥፋታቸውም ሥረየትን በጠየቁ ጊዜ  እግዚአብሔር ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ተስፋቸውም 5500 ዘመን ሲፈፀም ከልጅ ል ህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚል ነበር። ይሄን ተስፋ ለመፈፀም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ፴ ዘመን ሲሞላው በዮርዳኖስ ተጠመቀ።

የተነገረው ትንቢትና የተቆጠረው ሱባኤ ሲፈጸም በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ የዕዳ ደብዳቤውን እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደሰውነቱ ረግጦ አጥፍቶልናል። በሲኦል ያስቀመጠውንም በእለተ አርብ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ አጥፍቶል።

ታቦቱን ተሸክሞ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ ምሳሌ ሲሆን ታቦቱ የጌታችን ምሳሌ ነው፤ ምሳሌነቱም ዮሐንስ ታናሽ ሆኖ ሳለ አምላኩን እንዳጠመቀው፣ ካህኑ ደግም ቅዱሱን ታቦት ስለሚሸከም ነው።

ባሕረ ጥምቀቱ /የመጠመቂያው ውሃ/ የዮርዳኖስ ወንዝ ምሳሌ ነው።

ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው።

ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መውረዱና በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው  ምሮ ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ሲያስረዳ፤ ቅዳሴ ስረዓቱ በሌሊት መሆኑ ጌታችን የተጠመቀው ሌሊት ላይ መሆኑን ሲያጠይቅ ነው።

ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበርድ ወር ነው። በዛ ብርድ ከወንዙ ዳር እንዲሁ ውሎ ማደር ስለሚያስቸግር፤ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር። ዛሬም በሀገራችን በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖችና ዳሶች ይጣላሉ።

ጥምቀት በብሉይ ኪዳን

በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን ያመሰገኑ ነበር። … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ልደተ ክርስቶስ

“ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምዪዮ ስሞ ኢየሱስ”
“እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ሉቃ ፩÷፴-፴፩

Lidet Flyer_2010_2ndበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ደንብ መሠረት ፱ ዓበይት በዓላት አሉ። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ደግሞ ከ፱ኙ ዓበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው።
በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ዕፃ በቤተልሔም ጌታ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ እነሆ የፍልስፍና ሰዎች ከምሥራቅ መጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው እያሉ (ማቴ ፪፥፩–፲፪)። እሊህ ፈላስፎች ከበልዓም ወገን ናቸው። እነርሱም በከዋክብት የሚፈላሰፉ ነበሩ። በመጽሐፋቸው በበልዓም መጽሐፍም የአይሁድ ንጉሥ ሊወለድ እንዳለው ተጽፏል። እርሱ በልዓም ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤልም ንጉሥ ብሎ ነበርና። ታዲያ እግዚአብሔር በረቀቀ ጥበቡ ይህንን ኮከብ ገለጠላቸው፡፡ በአዩትም ጊዜ ደስ አላቸው መልኩ በብዙ ዓይነት ልውጥ ነውና። ሕፃን የታቀፈች ድንግል ብላቴናን ይመስላል እርሱም በቀን ይጓዛል በሌሊትም የሠወራል ከሰውም ሲገናኙ ይሠወርና ሲቆሙ በሌላ አንጻር ይገለጥላቸዋል። እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኮከቡ ተሠወራቸው፡፡ እጅግም አዘኑ የሚያደርጉትንም አላወቁም። ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ስለ ተወለደው ንጉሥ ጠየቁ። ይህን በሰማ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ደነገጠ፡፡ የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጸሐፊዎች በሙሉ ሰብስቦ ክርስቶስ በየት ይወለዳል ብሎ ጠየቃቸው። በይሁዳ ዕፃ በቤተልሔም ነው አሉት። በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና “ የኤፍራታ ዕፃ ቤተ ልሔም አንቺም ከይሁዳ ነገሥታት አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ የወለዳልና”።

ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ስለተረዳ ሕፃኑን ለመግደል በልቡ አስቦ ሄዳችሁ የዚህን ሕፃን ነገር እርግጡን መርምሩ ያገኛችሁትም እንደሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ ብሎ ወደ ቤተልሔም ሰደዳቸው። እነሆ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ወደ ቤተ ልሔም እስኪደርሱ ይመራቸው ነበር። ሕፃኑ ካለበት ዋሻ ደርሶ ቆመ። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ሕፃኑን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር አገኙት ወድቀውም ሰገዱለት ሣጥናቸውንም ከፍተው አምላክ ነውና ስለ መንግሥቱ ወርቅን ገበሩለት፡፡ ክህነትም ገንዘቡ ነውና ዕጣንን ገበሩለት፡፡ ማሕየዊ ለሆነ ሞቱ ምልክትም ከርቤን ገበሩለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ነገራቸው። በሌላ መንገድም ወደ አገራቸው ተመልሰው ገቡ። አምላክ በሥጋ ስለመገለጡ ዓዋጅ ነጋሪዎችና ሰባኪዎች ሆኑ።

በዚሁ ዕለት መላእክት በቤተ ልሔም ወደሚገኙ ጠባቆች ሄዱ። ወየዓቅቡ መራዕዪሆሙ ሌሊተ በበዕብሬቶሙ። በየፈረቃቸው ተግተው መንጋቸውን የሚጠብቁ፡፡ እሊህ ጠባቆች ዓሥራ ሁለቱን ሰዓተ መዓልት ካራት ተካፍለው ይጠብቃሉ። እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ባጠገባቸው ሲቆም ከቤተ ልሔም እነርሱ እስካሉበት ባሕረ ብርሃን ፈሰሰላቸው። ፈጽመው ፈሩ። መልአኩም አይዞአችሁ አትፍሩ እናንተንም ሰውንም ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ነገር እነግራችኋለሁ። መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የዓለም መድኃኒት የሚሆን የባሕርይ አምላክ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ በዳዊት ባሕርይ ተወልዷልና። ሕፃኑ አውራጣቱን ታስሮ በጨርቅ ተጠቅሎ በበረት ተጥሎ ታገኙታላችሁ አላቸው። ከእርሱም ጋር ብዙ መላእክት እግዚአብሔርን እንዲህ እያሉ እያመሰገኑ ሲመጡ ተሰሙ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፤ ወሰላም በምድር፤ ሥምረቱ ለሰብዕ”። አምላክ ለሆነ ሥጋ ከሥላሴ ጋራ በአንድነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ እያሉ፡፡ አንድም የሰው ፍቅር አገብሮት አምላክ ሰው ቢሆን ሰው አምላክ ሆነ፡፡ በዚህ የተነሣ በሰማያት በመላእክት ዘንድ ምስጋና ተደረገ። በደቂቀ አዳም ዘንድ አንድነት ተደረገ። መላእክት ከኖሎት፤ ኖሎት ከመላእክት ጋር አንድ ሁነው አመስግነዋልና እያሉ። እነዚህ ጠባቆች ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ እግዚአብሔር የገለጸልንን ነገር እንወቅ ብለው ሄዱ፡፡ በዚያም ዮሴፍን እና እመቤታችንን ሕፃኑንም በጎል ተኝቶ አገኙት የተነገራቸውም ስለ ሕፃኑ እንደሆነ አወቁ። ይህንን አይተው አደነቁ እነርሱም የነገሩዋቸው ሌሎች ሰዎች እነዲሁ አደነቁ። እንደ ነገሯቸው ስላዩት ስለሰሙት ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑት ጠባቆች ተመለሱ። እንዲህ ያለ ምሥጢር የገለጽክልን ተመስገን እያሉ።

“ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር”

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/አ/አ/ስ/የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ

                                                       ትምህርት ክፍል ተዘጋጀ

 

Training Materials

መልካም ዘመን

NASSU 2010 New Year Flyer_1የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ጥንት ከሚለው ቃል ይጀምራል፡፡ ጥንት የሚለው ቃል መገኛን መጀመሪያን ጀማሪንና አስጀማሪን ያመለክታል:: ለሀልዎቱ ጥንት የሌለው አምላክ እግዚአብሔር ዘመናትንና የዘመናትን መሥፈሪያ የሰጠን የዘመናት ባለቤት ነው፡፡ በባሕርዩም ፍጹም፣ ጥንትና ፍጻሜ የሌለው አምላክ ነው፡፡ ፍጥረት በመፍጠሩ ሥራውን የገለጠ በመሆኑ የተረዳ ሆኗል፡፡ ይኸውም እርሱ በወደደ በፈቀደ መጠን ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ፍጥረትን በመፍጠር /በሥራው/ ሲገልጥ ለፈጠረው ፍጥረት መለኪያ መወሰኛ ጊዜንም አብሮ ፈጥሮአል፡፡ ጊዜውንም በሰባት ዐበይት ምሕዋራት /መመላለሻዎች/ ከፍሎታል፡፡ እነዚህም ሰባቱ ዕለታት ናቸው፡፡

ዕለታት በብርሃንና በጨለማ ዑደት /መፈራረቅ/ እንዲታወቁ “ጠዋትም ሆነ ማታም ሆነ አንድ ቀን” በማለት የሥነ ፍጥረት ሥራዎቹን ያከናወነበትን አንድ ሳምንት በመቁጠር አመልክቷል፡፡ /ዘፍ.1÷1/ ብርሃንና ጨለማ ተፈራርቀው ዕለታትን በሰባቱ ምሕዋራት እየተመላለሱ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ረዥም ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ እግዚአብሔር የዘመን ቁጥርን በሥራው እንዳሳወቀን፤ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርም ዘመናትን በድርጊት ከፍሎ የታሪክ ዘመኑን በሁለት ጎራዎች ዘመነ ብሉይ ዘመነ ሐዲስ ወይም ዓመተ ዓለም እና ዓመተ ምህረት እያለ ይቆጥራል፡፡

ዘመነ ብሉይ /5500 ./ ለመላው የሰው ልጅ መልካም የሚባል ጊዜ አልነበረም፡፡ በዲያብሎስ እስራት እየማቀቀ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን እየተጠባበቀና እየናፈቀ የኖረበት ዘመን ነበርና፡፡ ስም አጠራሩም ዘመነ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ . . . የሚባል ነበር፡፡

ርግበ ኖኀ የጥፋት ውኃ መጉደሉን የጥፋት ጊዜ ማለፉን ታበስር ዘንድ ለምለም ቅጠል ይዛ እንደተመለሰች፡በቀዳማይ ሺህ ዓመት መግቢያ ላይ በነቢይ “ቃለ ዐዋዲ” ተብሎ የተነገረለት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የአዲስ ዘመን ዜና ብሥራትን ነገረን፡፡ “የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ..” በማለት የመጻኢውን ዘመን ብሩህነት፣ መልካምነትና የለውጥ ዘመንነት ለማየት ለሚወድዱ ሁሉ በንስሐ ጥምቀት እንዲዘጋጁ ሰበከ፡፡ /ማር.1÷2/

ከመጥምቁ ዮሐንስ ቀጥለው የዚህን ዘመን /የዘመነ ሐዲስን/ ዜና ብሥራት ለሰው ልጆች የነገሩ የሰማይ መላእክት ነበሩ፡፡ “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት .. ተወልዶላችኋል” የሚለው የመላእክት የደስታ መግለጫ ቃል “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” በሚለው ዝማሬ መላእክት የታጀበ ነበር” /ሉቃ.2፥14/:: ክርስቲያኖች ከመላእክተ እግዚአብሔር በተማርነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት /ውርስ/ አማካኝነት፤ ለሰው ወገን ሁሉ የመልካም ምኞት መግለጫችንን በልዩ ልዩ መንገድ “መልካም ዘመን” እያልን እንገልጻለን፡፡ ቃሉ የታወቀና ሕፃናትና አዋቂዎች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የእምነት አባቶች እና ሌሎችም በዘመን መለወጫ በዓል የማይዘነጉት ነው፡፡

እድሜአችን ላይ ይህን አዲስ ዓመት በየጨመረልን እግዚአብሔር በቅዱስ መጽሐፉ አማካኝነት “መልካም ዘመን” ይለናል፡፡ አዲስ ዘመን የሰጠን የዘመናት ባለቤት ፈቃዱን ፈጽመን የርስቱ ወራሾች የምንሆንበትን የንስሐ ዘመን ጨምሮልናል ፤ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ በሚፈጥንና በሚያልፍ ጊዜ ውስጥ ወደማያልፍ ክብርና ዓለም የሚያሻግረንን ሥራ የምንሠራበትን “ዓመተ ምህረት” አቀናጅቶናል፡፡ /መዝ.64÷11/ … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ