በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ለኢ.ኦ.ተ. ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

ለዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት

ለኒውዮርክ ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት

የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች ይልቅ ኃያላን ናቸውዘፍ 49 26

         ከተራራና ከሸለቆ፣ ከማዕበልና ከወጀብ ይልቅ ኃይል ያለውን በረከትና አንድነት ይዛችሁ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ የተቀመጣችሁ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን ሆይ ከ26 ዓመታት በላይ የቆየውን ሲኖዶሳዊ ልዩነት ወደ አሃዳዊ ሲኖዶስ በማምጣት በአንድነት በአንድ መንበር ሥር ለመቀመጥ በመቻላችሁ እጅግ ደስ ብሎናል። መላው ሕዝበ ክርስቲያንም ይህንን ከባድ ውሳኔ በወሰናችሁና ባጸናችሁ አባቶቻችን ተደስቷል። ታሪክ የማይረሳውና ትውልድ የሚኮራበትን ሥራ ሠርታችኋል፤ በፊታችን የነበረውን ከባድ ድንጋይ አንከባላችሁልናልና በእናንተ ደስ ብሎናል። ከምንም በላይ ደግሞ እግዚአብሔርን አስደስታችኋል።

          ባሳለፍናቸው 26 ዓመታት የነበረው የአባቶች ልዩነት ተፈትቶ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ በሀገር ውስጥም ከአገር ውጭም የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት በአንድ ጉባዔ ይቀመጣሉ። በዚህ አሃዳዊና የመጀመሪያ በሆነ ታሪካዊ ጉባዔ እጅግ ወሳኝና ጠቃሚ፤ አስቸኳይና ዘመኑን የዋጁ አጀንዳዎችን በማስቀደም ለቤተክርስቲያን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮች ውሳኔ እንደምታሳልፉ እንጠብቃለን።

           በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ በሀገረ ስብከት ደረጃ ተመድበው ከሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን በውጭ ያለችውን ቅድስት ቤተክርስቲያን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትንና፣ አብነት ት/ቤቶችን በተለይም ድንገተኛ የእሳት አደጋ በደረሰባቸው ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ላይም ፈጣን እርዳታ በመስጠት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የገጠር ሰንበት ት/ቤቶችን አቅም በማስቻል ሥራወች ላይ ለ19 ዓመታት ያህል ሲያገለግል እንደቆየ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ከተመሠረተው አገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት ጋር በመሆንም የበኩሉን አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህን ለዘመናት ስንጠብቀው የነበረውን የአባቶች አንድነት እውን እንዲሆን ለማድረግ በነበረው እረጅም ጉዞ አንድነት ጉባዔው የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።

           የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ ከዕርቀ ሰላሙ በኋላ በዚህ የመጀመሪያ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ እየተንከባለሉ ለቆዩት እና ዛሬ ላይ ለደረሱት የተለያዩ የቤተክርስቲያናችን ችግሮች የመፍትሄ ውሳኔ ይጠብቃል። በዚህ የመጀመሪያ ጉባዔ ሁሉንም ጉዳዮች ባያነሣና መፍትሄ ባይሰጥ እንኳ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የሚጠበቁት ሥራዎች ግን ምን ያህል ሰፊና አስፈላጊ መሆናቸውን በመገንዘብ ወጣቱ ምን ያህል የመፍትሄ ውሳኔዎችን ከአባቶቹ እንደሚጠብቅ ማስታወስ ተገቢ ነው።

           የቤተክርስቲያንን ማዕከላዊ አወቃቀር በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመሥራት መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥራ ዘርፎችን ጨክኖ መለየት ያስፈልጋል። ይህ መንፈሳዊውን የአገልግሎት ዘርፍ ከአስተዳደራዊው ዘርፍ የመለየቱ ሥራ ለጊዜው አስቸጋሪ ቢመስልም ለነገዋ ቤተክርስቲያን ግን የማዕዘን ድንጋይ እንደ ማስቀመጥ ነው። ባለፉት 40 ዓመታት የነበሩት የተለያዩ የቤተክርስቲያናችን ፈተናዎች በጊዜው በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ የተፈጠሩ ስለነበሩ እጅግ በርካታ ምእመናንን አሳጥተውናል በርካታ የታሪክ ጠባሳዎችንም ፈጥረውብናል። ካሁን በኋላ ለሚመጣው ፈተና ግን ቅድመ ዝግጅትና ዘመኑን የዋጀ የመፍትሄ መንገዶችን ማዘጋጀት የዚህ አሃዳዊ ሲኖዶስ የሥራ ድርሻ ነው።

           መንፈሳዊና አስተዳደራዊ የሥራ ዘርፎች ከተለዩ በኋላ የሚሠሩት ሥራዎች እጅግ ብዙዎች ናቸው፦ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በቂ የሆነ ሀገረ ስብከት ማቋቋም፣ በሀገረ ስብከት የሚመደቡ ሊቃነ ጳጳሳትን በፈቃድና በውዴታ ምደባቸውን እንዲቀበሉ ማድረግ፣ በተለይም በውጭ ላለችው ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶሱን ሙሉ እይታ መስጠት፣ በውጭ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን እውነተኛና ዘላቂ በሆነ መዋቅር ከሀገረ ስብከቶቻቸው ጋር ማዋቀር፣ ሰንበት ት/ቤቶችን ከአደረጃጀታቸው ጀምሮ መከታተልና እንዴት በአንድነት ማገልገል እንዳለባቸው አቅጣጫ ማስቀመጥ፣ የደብር አስተዳዳሪዎችን የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎችንና የተለያዩ የክፍል መምሪያ ኃላፊዎችን በአስተዳደራዊ ትምህርት/Management course/ በማሰልጠን አግልግሎታቸውን በእውቀት ማገዝ፣ የባለሙያ ማሰተባበሪያ … ሙሉ መግለጫውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ!!!

በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነት እና የበረከት ይሁንልን!!!

ነገረ መስቀል

መስቀል በዘመነ ኦሪት የወንጀለኛ መቅጫ (መግደያ) ሆኖ ያገለግል ስለነበር በብዙዎች ዘንድ በመጥፎነቱ እና በአስፈሪነቱ ይታወቅ ነበር። በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት የተፈረደበትም የተረገመ፤ የተጠላ እና ከፍተኛ ወንጀል የሠራ በመሆኑ መስቀል የእርግማን ምልክት ሆኖ ይቆጠር ነበር። በአዲስ ኪዳን ግን ንጹሐ ባህሪይ ክርስቶስ ለድህነተ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ በመለኮታዊ ደሙ ስለቀደሰው የእርግማን ምልክት የነበረው፤ የድል ምልክት፤ የሞት ምልክት የነበረው የሕይወት፤ የሰላም፤ የፍቅር እና ለክርስቲያኖች የድል ምልክት ሆኗል። መስቀል በመጽሐፍ ቅዱስ በሦስት ይከፈላል።፡ይኸውም፡

  1. መከራ መስቀለ ክርስቶስ
  2. መከራ መስቀለ ክርስቲያን
  3. ዕፀ መስቀል ናቸው።

1- መከራ መስቀለ ክርስቶስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ከጎልጎታ እስከ ቀራንዮ አደባባይ ከዚያም እስከ ርደተ መቃብር የደረሰባት ስለ ሰው ልጆች ድህነት የተቀበለው ጽኑ መከራ መስቀል ይባላል። ጌታ መድኃኒት ክርስቶስ ንጉሥ ሲሆን በበረት መወለዱ፤ በጨርቅ መጠቅለሉ፤ በብርድ ወራት መንከራተቱ፤ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ምድረ ግብፅ በሐሩር ሙቀት በአሸዋ ግለት ተሰደደ። እኛን ከስደተ ነፍስ መመለሱ ጠላታችን ሰይጣንንም ከሰዎች ልቡና ማሳደዱ፤ የአይሁድን ስድብ እና መዘባበት መታገሱ፤ በአውደ ጲላጦስ መወቀሱ፤ ከለሜዳ መልበሱ፤ የእሾህ አክሊል በራሱ መድፋቱ፤ በበትር መመታቱ፤ በቀኖት መቸንከሩ፤ በጦር መወጋቱ፤ መጣጣ መጠጣቱ፤ በእንጨት ላይ መሰቀሉ… በአጠቃላይ ስለ ድህነተ ዓለም የተቀበለው መከራ መስቀል ይባላል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዎሎስም “የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለምናምን ለእኛ የእግዚአብሔር ኃልይ ነው” ሲል አስረግጦ ይመሰክርልናል (1ኛ ቆሮ 1፤8)። ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ፅንአ ነፍሳችን ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ አይሁድ መከራው ለእኛ አይደለም ብለው ካዱት። እኛ ግን አመንን። ስላምንም በመስቀሉ ኃይል ዳንን በማለት ታስተምረናለች። በዚህም ምክኒያት መስቀል የክርስቲናያኖች ሁሉ መመኪያ እና የሰላም አርማ ሆኗል (ገላ 6፤1 ኤፌ 2፤16)።

2- መከራ መስቀለ ክርስቲያን

አንድ ክርስቲያን ወይም ሐዋርያ ስለ ክርስቶስ ስም፤ ስለ ወንጌል፤ ስለ ቤተርክርስቲያን፤ ስለ ማኅበረ ምአመናን የሚደርስበት መከራ፤ ስድብ፤ ሐሜት፤ ስቅላት፤ ግርፋት፤ መሰደድ…ወዘተርፈ መስቀል ይባላል።፡ጊታችን በወንጌል ሲናገር “መስቀሉን የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባወም” (ማቴ 10፤36) ይላል። እንዲሁም በሌላ የወንጌል ክፍል “ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16፤24 ማር 8፤34-36) ይላይ። እዚህ ላይ ጌታ ሲናገር “መስቀሌን” ሳይሆን “መስቀሉን” ተሸክሞ ይከተለኝ ማለቱን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ቅዱስ ጳውሎስ በሰይፍ መመታቱ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል መሰቀሉ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጋዝ መሰንጠቁ፤ የቅዱሳን ልዩ ልዩ መከራ መከራ መስቀል ይባላል።

3-   ዕፀ መስቀል

ዕፀ መስቀል ስንል ከእንጨት የተሰራ መስቀል ማለታችን ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ያዳነን በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ፤ ደሙን አፍስሶ፤ ቅዱሳን እጆቹን እና እግሮቹን ተቸንክረውበት ሰይጣን እና አሠራሩ በመስቀል ስለተደመሰሱበት ቅዱስ መስቀል ብለን እንጠራዋለን።  … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

በኢትዮ ሶማሌ ሀገረ ስብከት ለተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተጐዱት ካህናትና ምእመናን የርዳታና የመልሶ ማቋቋም ጥሪ

በኢትዮ ሶማሌ ሀገረ ስብከት በተፈጸመው ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ለተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተጐዱት ካህናትና ምእመናን የርዳታና መልሶ ማቋቋም አስተባባሪ ኮሚቴ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሰብሳቢነት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ደረጃ መቋቋሙ ይታወሳል፡: በተከሰተው ግርግርና ግጭት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ካህናትና ምእመናን ተገድልዋል፤ ንዋየ ቅድሳት ተዘርፈዋል፤ የአብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ምእመናን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡

በደረሰው ጉዳት 10 ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ መንበረ ጵጵስናው፣ የአብነት ት/ቤት ጉባኤ ቤቶች፣ የአጥቢያ ገቢ ማስገኛ ሕንጻዎች እና ሌሎች ንብረቶች ተቃጥለዋል፤ በርካታዎችም ተዘርፈዋል፡፡ እንዲሁም 8 ካህናት ተገድለዋል፡፡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ምእመናንና አገልጋዮች ከአጥቢያቸውና ከመኖሪያ ይዞታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱን ወደ ነበሩበት ይዞታ መመለስ ይቻል ዘንድ፤ መኖሪያ በታቸውና ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖቻችንን ለዘለቄታው ለማቋቋም፤ እንዲሁም የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ካጋጠማቸው የከፋ አደጋ ለመታደግ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ከተዋቀረው አስተባባሪ ኮሚቴ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል፡፡ ከደረሰው ጉዳት አንጻር አብያተ ክርስቲያናቱን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑና ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወገኖችን በድጋፉ ላይ ለማካተት ይቻል ዘንድ ይህ የGoFundMe ገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገድ በብጹዕ አባታችን አቡነ ፋኑኤል የዋሺንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልካም ፈቃድ ተከፍቶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ይህንን የገቢ ማሰባሰብ ሂደት በሰሜን አሜሪካ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ስር የሚገኙ መንፈሳውያን ማኀበራት በሰሜን አሜሪካ የካህናት ማኀበር፣ በሰሜን አሜሪካ አኀጉረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ፣ በማኀበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማዕከልና በሰሜን አሜሪካ አኀጉረ ስብከት የማኀበረ በዓለወልድ በመቀናጀት የሚያስተባብሩት ሲሆን የሚሰበሰበው ገንዘብ ተሰብስቦ እንዳለቀ ለዚህ አገልግሎት እንዲውል በኢትዮጵያ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ የሚያስገቡ ይሆናል:: በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ አብያተ ክርስቲያናቱን ወደ ነበሩበት ይዞታ መመለስ ይቻል ዘንድ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደረግ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡

Please click here to support Help Jigjiga Churches & Victims

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ለኢ.ኦ.ተ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስና ብፁዐን አበው በሙሉ

ለዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

ለኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

ከሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ

”ለመራቅ ጊዜ አለው ለመተቃቀፍም ጊዜ አለው” መክ ፫፥፮

ከዘመናት አስቀድማ ይልቁንም በተገለጠ አቆጣጠር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በሕገ ኦሪት እግዚአብሔርን ስታመልክና ስትታዘዝ የነበረች ሀገራችን ኢትዮጵያ በ፬ኛው መ/ክ/ዘ ክርስትናን ብሄራዊ ሃይማኖቷ አድርጋ መቀበሏ ለሁሉም የተገለጠ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም የተሰጣትን ኃላፊነት በሃይማኖት፣ በምግባር፣ በታሪክ፣ ማንንነቱን የሚያውቅ ትውልድ በመቅረጽ፣ በቋንቋና ባህልን በመጠበቅ ረገድ ተቆጥሮ የማያልቅ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች። ባለፉት ፪፮ (26) ዓመታት ግን በሃይማኖት አባቶች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ሆኗል። በጊዜው የተፈጠረው ልዩነት በቤተክርስቲያናችን ላይ አስተዳደራዊ ብሎም ቀኖናዊ ለውጥ እንዲከሰት አድርጎ ልዩነቱን ሲያሰፋና ሲያባብስ ቆይቷል። በዚህ የተፈጠረው አስተዳደራዊና ቀኖናዊ ችግር ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ሆኖ ቆይቷል።

አባቶቻችን ሆይ ከምንም በላይ ከ፪፮ (26) ዓመት በፊት ሕፃናት ስለነበሩትና ዛሬ ወጣት ሆነው በሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ውስጥ ስለሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ተተኪዎች ማሰብ ተገቢ ነው። በልዩነቱ ውስጥ እንዲያድጉ በተደረጉና በውጩ ዓለም በተወለዱ የቤተክርስቲያን ልጆች አእምሮ የተፈጠረው ሃይማኖታዊ ቀኖናዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር እጅግ የሚያሳዝን ነው። ምናልባትም የተለያዩ ምክኒያቶችን በማስቀመጥ ልዩነቱ እንዲቀጥል ማድረግ በአንድ ትውልድ ላይ ሞት የማወጅ ያህል ነው። ከምንም በላይ የችግሩን ጥልቀት የምትረዱትና ችግሩ ሲፈጥር በቦታው የነበራችሁ አባቶች በሕይወት እያላችሁ ለችግሩ መፍትሄ መስጠታችሁ እጅግ ተገቢ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እንደሚደግፈው በግልጽ ያሳወቀ ስለሆነ ይህንን እድል በመጠቀም የቤተክርስቲያናችንን አንድነት ወደ ቀደመ ክብሯ በመመለስ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንድታስረክቡን እንማጸናለን። በመራራቅ የቆየንበት ያለፈው ዘመን ይብቃና ቀሪው ዘመን የመተቃቀፍ የሆንልን ዘንድ አባታዊ ቃላችሁን በመቃተት እንጠብቃለን።

አባቶቻችን ሆይ በቃልም በመጽሐፍም ስለ አንድነት ስለ ፍቅር ስለፈተና እና ተመዝኖ ስለማለፍ አንድም ሳታጎሉ አስተምራችሁናል። አሁን ደግሞ የተማርነውን በተግባር የምናየበት ጊዜ ነው። በታላቅ ናፍቆትና ጉጉትም እየጠበቅን እንገኛለን። በሰንበት ት/ቤት የምንገኝ ወጣቶች ዘመኑን የዋጀ ሥራ ለምሥራትና የቤተክርስቲያናችንን አግልግሎት ለማስፋት በአባቶቻችን በኩል ያለው ልዩነት ትልቅ የእንቅፋት ድንጋይ ሆኖብናል። ታዲያ ከእናንተ ከአባቶቻችን ውጭ ሌላ ማን እንቅፋቱን ሊያነሳልን ድንጋዩንስ ሊያንከባልልን ይችላል!?? ወጣቱ ከምእመኑ ጎን በመቆም የተስፋ ዐይኑን በእናንተ በኩል ወደ እግዚአብሔር አንሥቷልና አታሳፍሩን።

የእናንተ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር መልካም ተስፋን ሁሉ ሲፈጽም እናውቀዋለንና ተስፋችንን ይፈጽምልን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን።

በረከታችሁ ጸሎታቹሁና ቡራኬያችሁ ከእኛ ጋር ትሁን አሜን!

 

 

                       በኢ.ኦ.ተ.ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት

                       የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ ሥራ አመራር

                                                ሐምሌ 8/2010 / July 15/2018

ግልባጭ

* ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በያሉበት

* ለኢትዮጵያ አገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት

* ለዩናይትድ ኪንግደም የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

  Please click here for PDF version …