እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የዕርገት በዓል አደረሳችሁ!!!
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ” (ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)ዕርገትጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ አምላካችን ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ የገባላቸው ቃልኪዳን፡ 1. ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡ (ሉቃ 24÷48) ደቀመዛሙርቱ ያዩትንና የሰሙትን ሞትን አሸንፎ የተነሣውን ጌታ ለዓለም ሁሉ ምስክሮች ሆነዋል። በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የዓላውያንን ነገሥታት፣ የቄሳሮችን ዛቻና ማስፈራሪያ አንዳችም ሳይፈሩ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ ድረስ ሁሉን እያጡና መከራ እየተቀበሉ፣ እየታሰሩና እየተገረፉ ምስክሮች ሆነዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ በኋላ ስሙን አትጥሩና በስሙም አታስተምሩ እያሏቸው በሸንጐ ፊት ሲያቆሟቸው፣ ሲገርፏቸው ደስ እያላቸው ከሸንጐ ፊት ይወጡ ነበር፡፡ (የሐዋ 5÷40)። ስለ ስሙ ምስክር መሆን መነቀፍና መታሰር፣ መደብደብ እንዴት ደስ ይላል!። እኛም እንደ ደቀመዛሙርቱ ማንንም ሳንፈራ አፋችንን ሞልተን ስለ ስሙ እየመሰከርን ሁሉን ብናጣም ሞታችንን በሞቱ ድል የነሣልንን የሚቃወመንን ጠላታችንን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያስወገደልንን፣ እረፍትና ሰላም የሰጠንን፣ ጨለማውን ገፎ ብርሐንን ያጐናፀፈንን፣ ያለፈውን ታሪካችንን በነበር ላስቀረልን ምስክሮች እንሁን። 2. አጽናኙን እልክላችኋለሁ (ዮሐ 15÷26)፡- 3. በኢየሩሳሌም ቆዩ ኃይልም ታገኛላችሁ (ሉቃ 24÷49)፡- ደቀመዛሙርቱ ከቢታንያ ወደ እኛ ሰማያዊ ኃይል ለማግኘት የት እንቆይ? በአንድ ልብ ሆነን በቤታችን፣ በአገልግሎታችን፣ በዘር፣ በጐሣ ሳንከፋፈል ይኸ እንዲህ ነው፣ ያ ደግሞ እንዲያ ነው፣ ሳንል ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ሳንወጣ የወጣንም ተመልሰን በኅብረት ሆነን መቆየት ያስፈልገናል። ማጠቃለያ አምላካችን የማዳን ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለተከታዮቹ ደቀመዛሙርት ምስክሮቼ ናችሁ። አጽናኙን እልክላችኋለሁ። “አንትሙ ንበሩ በሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ሃይለ እማርያም፡፡ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ አዘዛቸው። በመጨረሻም ወደሰማይ ሲያርግ እጆችንም አንስቶ ባረካቸው። (ሉቃ 24÷51) ስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፡- ከኢትዮጽያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱሳት መጻህፍቶች እና ስብከቶች የተውጣጣ |
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። *** ዕለተ ሆሣዕና *** “እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።” ት. ዘካ. 9፥9 የዐቢይ ጾም ስምንተኛውና የመጨረሻው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል። ቀደምት ነቢያት ዘመነ መዓት መምጣቱን ለማስታወቅ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው / ጦር አንስተው/ በከተማ ሲዘዋወሩ የሚታዩ ሲሆን ዘመነ ምሕረት መምጣቱን ለማሳየት ደግሞ በአህያ ላይ ተቀምጠው ይታዩ ነበር። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሕዝበ እስራኤል የተለመደውን ሥርዓተ ነቢያትን በመጠቀም በሰውና በእግዚአብሔር ፣ በሰውና በመላእክት፣ በሥጋና በነፍስ፣ በተገዘሩት በሕዝበ እስራኤልና ባልተገዘሩት አሕዛብ መካከል የነበረው ጠብ ማብቃቱ ለመግለጥ እንዲሁም በነቢያት የተተነበየውን ሊፈጽም /ዘካ 9፥9/ በአህያና በውርጭላ ላይ በመሆን ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። በአህያ ላይ ተቀምጦ ከደብረዘይት ተራራ አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ደቀመዛሙርቱና ሕዝቡ ልብሳቸውን በማንጠፍ ሕፃናት ዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ ክብሩን መድኃኒትነቱን ገልጠዋል /ማቴ 2፥9፣ መዝ 8፥2 ፣ ሉቃ 19፥38/። ልብሳቸውንም ማንጠፋቸው፤ እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ እንኳን መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ልብሳቸውን አነጠፉለት። እነዚያ አይሁዳውያን ለተቀመጠባት አህያ ይህንን ያህል ክብር ከሰጡ፤ በድንግልና ፀንሳ ለወለደችው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምን ያህል ክብር ልናድረግለት ይገባን ይሆን? በዚህ ዕለት ፀበርት /ዘንባባ/ እየተባረከ ለሕዝብ ይታደላል ይኽንን በመያዝ ዕለቱ የፀበርት እሑድ ይባላል። አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፣ እስራኤል ዘሥጋ ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ዮዲት ሊወራቸው የመጣውን ሆሊፎርኒስ የተባለ የአይሁድ ንጉሥ በገደለች ጊዜ ዘንባባ ቆርጠው አመስግነዋል። ዘንባባ አንጥፈው ማመስገናቸው፤ √ ዘንባበ እሾኻም ነው የኃይል የድል ምልክት አለህ ሲሉ፤ √ አንድም ዘንባባ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አይበላውም አንተ ባሕሪህ አይመረመርም ሲሉ፤ √ አንድም ዘንባባ ረጅም /ልዑል/ ነው አንተም ባሕሪህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ አንጥፈው ተቀብለውታል። ሆሣዕና በዕብራይስጡ ‹‹ሆሼዕናህ›› የሚል ሲሆን ‹‹እባክህ አሁን አድን›› ማለት ነው። መዝ 117(118)፥25-26 ኢየሱስ በሕዝቡ እልልታና ደስታ ታጅቦ ሲገባ ተጠንቅቀው ይታዘቡትና ይመለከቱት የነበሩ ፈሪሳውያን ደቀመዛሙርቱን ዝም እንዲያሰኛቸው ተናገሩት። እርሱም ሕዝቡ ዝም ቢል ድንጋዮች እንደሚጮኹ አስታወቃቸው። ኢየሱስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከተማዪቱን አይቶ አለቀሰላት እንዲህም አላት። “አንቺስ ብታውቂ ሰላሽ ዛሬ ነበረ ከእንግዲህ ውዲህ ግን ከዓይኖችሽ ተሰወረ … የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና” /ሉቃ 19፥41-44/። … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ |
የአብነት ትምህርት ገጽ | ወቅታዊ ጽሑፍ | ትምህርት ክፍል የሥራ እንቅስቃሴ የመጠይቅ ቅጽ |