111

 እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረስዎ!

  ጥምቀት ምንድን ነው?

timiket picጥምቀት ማለት ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፤ መነከር፤ መዘፈቅ፤ መጥለቅ ማለት ነው። ጥምቀት ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን (ምስጢረ ጥምቀት፤ ምስጢረ ሜሮን፡ ምስጢረ ቁርባን፤ ምስጢረ ንስሐ፤ ምስጢረ ክህነት፤ ምስጢረ ተክሊል፡ እና ምስጢረ ቀንዲል) አንዱ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐ. 3፥5 ላይ “እውነት እውነት እልሃለው፤ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስቅዱስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሎ እንደተናገረው ከውኃ እና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት፤ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት፤ ኃጢአያታችን የሚደመሰሥበት፤ ድኅነትን የምናገኘበት ዐቢይ ምስጢር ነው። ጥምቀት በምስጢረ ሥላሴ እና በምስጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ፤ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው።

                             የጥምቀት አመጣጥ

የምስጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠቀሙበት ጥምቀት ነበራቸው። ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን በማጠብ የእግዚአብሔር ቤት መገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ የማጠብ እና የማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር። የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበረባቸው። ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምስጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር። “አሮንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ” (ዘፀ29፥4)። “ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፤ በውኃም አጠባቸው” (ዘሌ 8፥6)

 በብሉይ ኪዳን ዘመን የጥምቀት ምሳሌዎች

1.  አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው። አብርሃም የምእመናን፤ መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው። (ዘፍ 14፥17/ ዘሌ 15፥8)

2. ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል። ይህም ምዕመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው።

3. ንእማን ሶሪያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል። 2ኛ ነገስት 5፥14 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው።

4. የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው። ዘፍ 6፥13። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው። አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል። ሥጋን ከዕድፍ በማጠብ ሳይሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሳቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ። 1ኛ ጴጥ 3፥20

5. እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው። (ዘፀ 14፥15)። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ። ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ። ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመና እና በባሕር ተጠመቁ” 1ኛ ቆሮ 10፥1-2።

6. ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው። አብርሃም ካረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር (ዘፍ 17፥9)። “የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ፤በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ” (ቆላ. 2፥11-13)።

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?

1. ምስጢርን ለመግለጥ፦ ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልፅ ሆኗል። አብ በደመና “የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፤ መንፈስቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ። ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ። ስለዚህም ምሥጢርን ለመግለጽ ስንል የአንድነት ሦስትነት ምስጢር በጎላ ሁኔታ ታወቀ ማለታችን ነው። (ማቴ. 3፥16)። … ተጨማሪ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

flyer_regis_comp-3-termወደ አብነት ትምህርት ገጽ ለመሄድ እዚህ ያጫኑ

 

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች

አንድነት ጉባኤ 16ተኛ ዓመታዊ ጉባኤ

ከነሐሴ 27-29, 2008 ዓ/ም

በዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል

ከአርብ ነሐሴ 27 ጀምሮ ለ 3 ቀናት የቆየው ይህ ዓመታዊ ጉባኤ ከ 23 የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ ተሳታፊዎች የተገኙበት ሲሆን አርብ ምሽት ከዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው በተሰባሰቡ ካህናት አማካይነት በጸሎት የተጀመረ ሲሆን በተከታታይ ለሁለት 2 ቀናት   ስብከተ ወንጌል፣ ዓመታዊ ሪፖርት፣ ጥናታዊ ጽሁፎች ፣የክፍለ ግዛት እንቅስቃሴዎች ግምገማ እና ሪፖርት፣ ዝክረ ያሬድ፣ መንፈሳዊ ድራማዎች እና መዝሙራት እና ሌሎችም መርሃ ግብሮች ቀርበዋል። ላለፉት 4 ዓመታት በመሳተፍ ላይ የሚገኙት መስማት የተሳናቸው ወገኖች በዚህ ዓመት ከተሳታፊነት ወደ መርሃ ግብር አቅራቢነት በመሻገር መስማት የተሳናቸው ወገኖች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርትም ሆነ ማንኛውንም መርሃ ግብር መሳተፍ እንዲችሉ አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጣቸው በድራማ መልክ መልእክታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተያያዘም በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚገኙ አዳጊ ወጣቶች በራስ ተነሳሽነት መንፈሳዊ ትምህርት የሚማሩበት፣ በጎ አድራጎት የሚያካሂዱበት እና ሌሎችንም ምግባረ ሰናይ ተግባሮችን ማድረግ የሚያስላቸው ማኅበር ያቋቋሙ ሲሆን ካህናት አባቶች በቅርብ ሆነው እንዲያስተምሯቸው፣እንዲመክሯቸው እና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትም በሚያስፈልጓቸው ነገር ሁሉ ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። ይህንን እና ሌሎችም አስተማሪ መርሃግብር ሲቀርብበት የነበረው የ3 ቀን ጉባኤ እሁድ ነሐሴ 29 ከምሽቱ በ 3:00 (9፡00 PM)ሰዓት በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዋሽንግተን ዲሲ እና የካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጸሎት እና ቡራኬ ተጠናቋል።

 

2008 Eastern Flyer

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ!

“ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም”

እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ (መዝ ፸፯÷፷፭ )

በቀሲስ አድማሴ መኮንን

          ታላቁ አባት ቅዱስ ኤፍሬም በሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፵፯ ክፍል ፩ ቁጥር ፮ ላይ ልዩ በሚሆን ድንቅ በሚያሰኝ መለወጥ ይስማማው በነበረ ሥጋ በተወለደው ልደት ወደ አልተለመደው ነገር /ወደ ሞት/ ወደ መስቀል ደረሰ (ኢሣ ፱÷፮ – ፯):: እኛን የሚመስል ሥጋን ገንዘብ አደረገ ይኸውም ከሁሉ ጋራ አንድ ነው ከባህርያችን የተገኘው አንድ አካል አንድ ባህርይ የሆነ እርሱ ሕማም ሞት የሌለበት ሲሆን በሥጋ ባህርይ ኃጥያት ሳይኖርበት ታመመ ሞተ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጥያት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጥአት አደረግነው(፪ኛቆሮ ፭÷፳፩)“ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ ኃሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሣለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማትን እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም ነገር ግን የባርያውን መለክ ይዞ በሰው ምሣሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ “ (ፊልጵ ፪÷፭-፱)“
         አምላክ ቃል በሥጋ እንደ ታመመ በሥጋ ተሰቅሎ እንደሞተ ከሙታን ተለይቶ ለሚነሣ በኲር እንደሆነ እሱ ሕይPic4ወትን የሚያድል እንደሆነ የማያምን ቢኖር እርሱ የተለየ የተወገዘ ነው አለ:: ምክንያቱም ትንሣኤ ሙታን እንዳለ ከሞት በኋላ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረት ሳይሆን መልካም የሠሩ ከመልካም ሥራቸው ጋር ለክብር ትንሣኤ ፤ክፉ የሰሩ ከክፉ ግብራቸው ጋር ለፍርድ ትንሣኤ ተነስተው እንደሚቀርቡ ዋጋቸውንም እንደሚያገኙ ያስገነዝበናል። ከአብ ተወልዶ የመጣ ቃልስ በመለኮቱ ሕማም ሞት የተለየበት ነው:: እርሱ ከህማም ከሞት የራቀ ነውና እርሱ ክቡር ነው:: የእግዚአብሔር ባህርይ የማይመረመር ነው:: እርሱ ለሁሉም ህይወትን የሚያድል ነው:: ይህ ባህርይ ከአብ ባህርይ የተለየ አይደለም ከአብ ጋር አንድ ነው እንጂ:: ስለ እኛ መከራን ይቀበል ዘንድ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሚታመም የሚሞት ሥጋን ለመዋኃድ ፈጠረ ሥጋንም ከእርሱ ጋር አንድ አደረገው:: ይኸው ለኛ ቤዛ ሆኖ መከራ ይቀበል ዘንድ ወደ እርሱ ያቀርበን ዘንድ ሞትን የተቀበለው ነው:: ሁላችንንም ከሞት ከፍዳ ያድነን ዘንድ አምላክ ነውና በባህርዬ ስልጣኑም ለሥጋ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ መከራ ተቀበለ:: ለሙታን በኲር ሆነ::
            ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድህነተ ዓለምን ከፈጸመ ቦኋላ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወረደ:: ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስበሶ መቅረትን ሊያስቀር ነው:: በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ ይኸውም ዲያቢሎስ በአዳም ላይ ያጸናው የባርነት ቀንበርን ሰበረ:: በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ነጻ ያወጣቸው ዘንድ ነው መለኮት በተዋህዶ ከሥጋም ከነፍስ ጋር ነበር:: ለዚህ ነው መቃብር ሥጋPic1ን ሊያስቀረው ያልቻለው ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለም /መዝ ፲፭÷ ፲ / ”ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱሱንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም ” ያለው ቅዱስ ጴጥሮስም ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ) እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ አመጸኞች አንድ ጊዜ በኃጥያት ምክንያት ስለ ሰው ልጆች ኃጥያት ተላልፎ በመሰጠት ሞትዋል በሥጋ ሞተ በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለየ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ ያን ሥጋ ነፍስ እንደተለየችው መለኮት አልተለየውም በእርሱ ደግሞ መለኮት በተዋሐዳት ነፍስ ሄዶ በወህኒ ለነበሩት ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው “እለ ውስተ ሲኦል ጻዑ ወለእለ ውስተ ጽልመት ተከሰቱ “ በማለት ከሲኦል እስራት ነጻ እንዲወጡ ከጨለማው ግዞት እንዲላቀቁ ነገረ ድህነትን ሰበካቸው አስተማራቸው:: 
ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት
በከርሰ መቃብር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት የቆየው በነቢዩ በቅዱስ ዳዊት ሥጋዬ በተስፋ ታድራለች በማለት የተናገረውን የትንቢት ቃል ሊስረግጠው እና ሊያጸናው ነው:: (መዝ ፲፭÷፱ ) ምስጢራዊ ትርጉሙም፦ ሦስት ሌሊት በመቃብር የወረደ መለኮት ነው ተስፋ ትንሣኤውም በተዋህዶ ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኮት ነው ነቢዩ ሆሴም “ ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ እርሱ ሰብሮናልና – በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነው እርሱ ፈውሶናል መርገመ ሥጋን አስወግዶ ከሞት ወደ ህይወት አሸጋግሮናልና እርሱ መትቶናል፦እርሱ ይጠግነናል ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል በሦስተኛው ቀን ያስነሳናል” በማለት አበው መተርጉማን ያመሰጥሩታል በሦስተኛው ቀን ትንሣኤው መሆኑን አረጋግጧል (ሆሴ ፮÷፲፪)። ይልቁንም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ከጻፎች ከሽማግሌዎች ከካህናት አለቆች ብዙ መከራ ይቀበል ዘንድ እና እንደሚገድሉት ከዚያም በሦስተኛ ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ነግሯቸዋል (ማቴ ፲፮÷፳፩) ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ በቀር ምልክት አይሰጠውም ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወል ዕጓለ ሕመያው ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል ብሏቸዋል (ማቴ ፲፪÷፴፰-፵ )
ሞትን ድል አድርጎ ስለ መነሣቱ፦
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የተነሣው በታላቅ ኃይል እና ስልጣን ነው:: ይኸውም የባህርይ ገንዘቡ ነው:: Pic5ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሳት ዘንድ) አኖራለሁ ( በፈቃዴ እሞታለሁ ) ስለዚህ አብ ይወደኛል እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር የለም ላኖራትም(በገነት ነፍሴን በመቃብር ሥጋዬን ላኖራቸው ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት) ሥጋዬን ነፍሴን አዋህጄ ላነሣት ስልጣን አለኝ በማለት አምላካችን ድንቅ የሆነ የባህርያ ገንዘቡ በሆነው አምላካዊ ሥራውን የገለጸው (ዮሐ ፲÷፲፯)።
        ታላቁ አባት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ” ተጨነቀ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም ሊታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም ” በማለት ተናግሯል:: እንዲሁ ይህም የትንቢት ቃል የሚያመለክተው በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ የትንቢት ቃል (ኢሣ ፶፫፥፯) ቅዱስ ጴጥሮስም በኃይሉ በስልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነስቷል እርሱ የትንሣኤ እና የህይወት ባለቤት ነውና ኢየሱስ “አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት ዘየአምን ብየ እመኒ ሞተ የሐዩ ወኩሉ ዘሕያው ወየአምን ብየ ኢይመውት ለዓለም (ኢየሱስም ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል”) (ዮሐ ፲፩÷፳፭) ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ቃል ብቻ አላበቃም የህይወትን እራስ ገደላችሁ በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው በኋላ እርሱን ግን እግዚአብሔር አስነሳው ለምን አለ? ለሚሉ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን አበው ቅዱሳት መጻሕፍትን አጣቅሰው አራቀው ትክክለኛውን ምስጢር ተርጉመው አስተምረዋል።
              እግዚአብሔር የሚለው የመለኮት መጠርያ ሲሆን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ሲጠራ ለዚህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫው ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ ወውእቱ ቃል ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ ቃል ወዝንቱ እምቀዲሙ ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ (ዮሐ ፩÷፪) ስለዚህ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው አንዲት በሆኑት በአብ በራሱ እና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሳ ተብሎ ይተረጎማል ይታመናል ትንቢያትም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው (ወተንስአ እግዚአብሔር ከመዘንቃህ እምንዋም ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለፀሮ በድህሬሁ) እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነሳ እንደሚነቃ ተነሳ የወይን ስካር እንደተወ እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹን በኋላው መታ (መዝ ፸፯÷፷፭)።
በአዲስ መቃብር ስለመቀበሩ፦
በእሥራኤል ባህል የአባቶቻቸው መቃብር ካረፈበት የመቅበር ልማድ አላቸው። ዮሴፍ እስራኤልን ልጆች እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንስታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ ያማላቸው የአባቶቹ የአብርሃም የይስሐቅ Pic3የያዕቆብ አጽም ካረፈበት መቃብር ፈልጎ ነው ( ዘፍ ፶፥፳፭ )።
ቤቴል የነበረው ሽማግሌም እንዲሁ ነበር የተናገረው (፩ኛ ነገ ፲፫፥፴፩)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ የቀበሩት እንደ እስራኤላውያን የቀብር ስርአት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት በአዲስ መቃብር ነበር ያም አዲስ መቃብር ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋውን በንጹህ በፍታ ከፈነው ከአለት በወቀረው በአዲስ መቃብር አኖረው በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ (ማቴ ፳፯÷፶፱) ይኽም የሆነው እርሱ ባወቀ በራሱ ጥበብ ነው እንዲህም በማድረጉ አይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል ምክንያቱም በ፩ኛ ነገ፲፫÷፪ የኤልሳዕ አጽም አጠገብ የተቀበራው አጽም በነካው ጊዜ እንደተነሳ በራሱ ጊዜ ሣይሆን የቅዱሱ አጽም ነክቶት ነው እንጅ እንዳይሉ ይህንን ምክንያት ለማጥፋት ነው በአዲስ መቃብር የተቀበረው።
በዝግ መቃብር ስለመነሣቱ፦ ጌታችንን ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኃላ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው ያ ሰው ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሎ በህይወቱ ያስተማረው ትዝ አለን እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ የኋለኛይቱ ስህተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት(ማቴ ፳፯፥፷፪-፷፮)። ጲላጦስም “እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው እነርሱም ድንጋዩን ከጠባቂዎች ጋር አትመው አስጠበቁ።
           ታላቁ አባት ሄኔሬዎስም በሃይማኖተ አበው ክፍል፪÷፳፯ ዳግመኛ ትንሣኤ ሙታንን በተናገረበት አንቀጽ በዲዲስቅልያ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የምንሆን እኛ ምእመናን በወንጌል እንዲህ እናምናለን አሉ የታመነ ነው በተናገረውም ሐሰት የለበትም መዝ፹፱ ዳዊት እግዚአብሔር በነገር ሁሉ የታመነ ነው በሥራውም ሁሉ እውነተኛ ነው ብሏልና ከንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ሥጋን ፈጥሮ የተዋሐደ እርሱ ነው ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ሙታንንም ሁሉ የሚያስነሣ እርሱ ብቻ ነው እንዳለው (ሮሜ ፩÷፫_፭) በመስቀል መከራ እንደ ተቀበለ እንደሞተ እንደተቀበረ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እንዳዩት ተናገረ።
               ቅዱስ አትናትዮስም ዳግመኛ እንዲህ አለ ፀሐይ ብርሃኑን በነሣ ጊዜ ፍጡራን ሁሉ በጨለማ ተያዙ የፈጠራቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሌባ እንደ ወንበዴ በእንጨት ተሰቅሎ እንዳያዩ ቀኑ ጨለመ ባለሟሉ መልአክም ዐላውያንን ያጠፋቸው ዘንድ ሰይፉን በእጁ መዝዞ ይዞ መላዕክት መካከል ወጣ የክርስቶስም ቸርነቱ በከለከላቸው ጊዜ ያ መልአክ የቤተ መቅደሱን መጋረጃ በሰይፉ መታው ቀደደው ከላይ እስከታችም ከሁለት አደረገው:: መላዕክትም ሁሉ ከሰማይ ሆነው እርሱን አይተው በአንድነት ሲቆጡ የአብ ምህረቱ የወልድ ትዕግስቱ የመንፈስ ቅዱስ ቸርነቱ ከለከላቸው ፀሐይ ብርሃኑን ነሣ ዓለምን በጨለማ ተይዞ ሲድበሰበስ ተወው:: ይህ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ከመለየቱ አስቀድሞ ተደረገ ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ብርሃን ታየ። ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ (መዝ ፸፫÷፲፪-፲፮ ፣ ፩ኛ ጴጥ ፫÷፲፰- ፳) ሲኦል ተናወጠች መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት:: ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውን ሁሉ ጠበቀ ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ተወው። ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወርዳ ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሣትን አዳነች:: ሲኦልንም በዘበዘች ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች:: ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ:: ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች። በዚያችም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ (ሊቃነ አጋንንት ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሱ)የብረት ቁልፎችም ተቀጠቀጡ (ፍዳ መርገም ጠፋ )ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃንን ነፍሳት ፈታች አለ:: ቴዎዶጦስ የተባለውም አባት “በህማሙ ህማምን ሊያጠፋ፣ በሞቱ ሞትን ሊያጠፋ የሰውን ህማም ገንዘብ አደረገ።” በማለት አስተምሯል:

አምላካችን እግዚአብሔር ከትንሣኤው ረድኤት በረከት ያሣትፈን!

የእናታችን ቅድስት ድንግልማርያም ምልጃ : የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤትና በረከት አይለየን።

ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብሔር ! አ ሜ ን

በቀሲስ አድማሴ መኮንን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ

YeLidet Flyer_2016

እግዚአብሔር አምላክ ሰውን የስሙ ቀዳሽ የርስቱ ወራሽ ይሆን ዘንድ ከምድር   አፈር አበጅቶ የሕይወት እስትንፋስ እፍ ብሎበት በአርአያውና በአምሳሉ በዕለተ ዓርብ ፈጠረው። ዘፍ 1፥26-28። በፀጋ የከበረ ሆኖ ፈጣሪውን እያገለገለ የተፈጠረበትን ዓላማ ለ7 ዓመት በመጠበቅ እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘ በክብር ኖረ። ዘፍ 2፥7። ዳሩ ግን በሰባተኛው ዓመት በሰይጣን ምክር አማካኝነት የተሰጠውን ሕግ አፍርሶ ዕፀ በለስን በላ፤ በዚህም ምክንያት ከክብሩ ተዋርዶ ከገነት ተባሮ በምድረ ፋይድ ተጣለ። ዘፍ 2፥16-17

ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ተፈረደበት። ዘፍ 3፥1-17። ባህርይው ጐሰቆለ፤ አዳምና ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ሆኑ። በእንዲህ ያለ ጽኑ ፍርድ ውስጥ እያሉ አዳም ስለበደሉ አዘነ፤ አለቀሰ፤ ፈጣሪውንም ይቅርታ ጠየቀ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በፈጠረው ፍጥረት ሳይጨክን “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚል የምሕረት ተስፋ ሰጠው። አዳምም ተስፋውን እየጠበቀ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል ምህረትን ሲናፍቅ ኖረ። ዘፍ 3፥16።

ቀጠሮው ሲደርስ ምን ሆነ?

የተናገረውን የማያስቀር የምህረት አምላክ አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ለአዳም አባታችን የገባውን ቃል ለመፈጸም ትንቢቱ ሲደርስ ምሳሌው ሲፈጸም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ እግዘአብሔር ከሴት (ከድንግል) የተወለደውን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከው” ገላ 4፥4 ዘፍ 3፥22 እንዳለው ለመዳናችን ምክንያት ከቅድስት ድንግል ማርያም መድኃኔዓለም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅም “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች እርሱም የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ” ሲል በሃይማኖተ አበው እንደገለፀው። ማቴ 1፥19–22፣ ኢሳ 7፥14፣ መዝ 2፥7 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር ታህሳስ 29 ቀን በዕለተ ማክሰኞ በድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ። ኢሳ 7፥14፣ ማቴ 1፥1-23፣ ሉቃ 2፥18። ……Click here to read more

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የሰሜን አሜሪካ የሰ//ቤቶች አንድነት ጉባኤ

የምስራቅ ክፍለ ግዛት ጉባኤ ህዳር 19, 2008 (Nov 29, 2015)

“አባቶት የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ”ምሳሌ 22፣28

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ትምህርት ቤቶት አንድነት (ሰ/አ/ሰ/ት/ቤ/አ) የምስራቅ ክፍለ ግዛት በዲሲና አከባቢው ለሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶት ኅዳር ፩፱, ፪፻፰ ዓ.ም (November 29, 2015) በምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት የደብሩ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ፍቅረማሪያም፤ የደብሩ ሰባኪ ወንጌል ቀሲስ ህብረት የሺጥላና የአጥቢያው ሰ/ት/ቤ/ወጣቶች በተገኙበት ልዩ መንፈሳዊ መርሐ-ግብር አዘጋጀ። ዕለቱ የተጀመረው በአባታችን ፀሎት ሲሆን በመቀጠል የደብሩ ሰ/ት/ቤ/ት መዘምራን መዝሙር አቅርበዋል።

በመቀጠል የክፍለ ግዛቱ ሰብሳቢ አበበ ለታ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በክፍለ ግዛቱ ሊተገበሩ የታቀዱ አስር ትግባራትን አብራርቷል። በክፍለ ግዛቱ ያሉ የሰ/ት/ቤቶች የሥራ አመራር አባላትን ማወያየት፤ ሦስት በአገልገሎት ደከም ያሉ ሰ/ት/ቤቶችን መጎብኘት፤ ሰ/ት/ቤቶችን ፋይል ማደራጀት ከተጠቀሱት የሥራ ክንውኖች ጥቂቶቹ ናቸው። በመቀጠል የዕለቱን የመርሃ ግብሩን መልእክት “አባቶት የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ” ምሳሌ ፪፪፣፪፰ በሚል ርእስ መምሀር ህብረት የሺጥላ ሰፋ ያለ ትምህርት አስተላልፈዋል። መምህሩ በውቅታዊው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሁላችንም ነቅተን እንድንጠብቅ አሳስበው በአንፃሩ ግን እነርሱ ስለራሳቸው ከሚሉት በላይ እኛ አግዝፈናቸው እንዳይሆን ማየት እንደሚኖርብን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የቤተክርስቲያን ልጆች በተለይም ሰንበት ተማሪ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት በአግባቡ ማወቅ እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰተው አሳስበዋል። ሥነ-ጽሑፍ ከደ/ም/ቅዱስ ሚካኤል ሰ/ት/ቤት እንዲሁም መዝሙር እና ሥነ-ጽሑፍ በመስማት በተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ከኆኅተ ምስራቅ ቅድስት ኪዳነምህረት ሰ/ት/ቤት ከዕለቱ ከተስተናገዱት መርሐግብሮች አካል ነበሩ። በማስከተልም የክፍለ ግዛቱ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በቀረበው የሦስት ወር እቅድ ላይ እንዲወያዩ መድረኩ ተከፍቷል። አባላቱም ሰ/ት/ቤቶች በነገው የቤተክርስቲያኒቱ ተረካቢዋች በሚሆኑት ህጻናት ላይ በደንብ መሰራት እንዳለበት ደጋግመው አሳስበዋል በተጨማሪም አንድ አይነትና ወጥ የሆን የአገልግሎት ሥርአት መዘርጋት እንዳለበት ጠይቀዋል። “ቤተ ክርስቲያንን አንተውም ከቶ” በማለት ከየሰንበት ት/ቤቶች ከተውጣጡ ሰንበት ተማሪዎች በመዘመር የመርሃ ግብሩ ፍጻሜ በምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤ/ክ/አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ፍቅረማሪያም ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል።   READ IN PDF

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር።

ማስታወቂያ

Flyer_Regis_Comp 2 term

NASSU Meskel Flyer 2008

“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትክ።” “በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ።” መዝ ፷፬፡፲፩

እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!

NewYearFlyer ከሁሉ አስቀድመን ዘመናትን በቸርነቱ አሳልፎ ለአዲሱ ዘመን  ያደረሰን፤ ንስሓ እንድገባ፤ በጎ ምግባር እንድናፈራ፤ብሎም ቀና አገልግሎት እንድንሰጥ ዕድሜ ያደለንን ልዑል እግዚአብሔር እያመሰገንን በያላችሁበት ክፍለግዛት የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት የምትተጉ አባቶቻችን፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ እንኳዋን ለ፳፻፰ ዓ.ም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ እንላለን። ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ በእግዚአብሔር ፈቃድ ያሳለፍነውን ጊዜ እንድንገመግም በመጭው ዘመን ከባለፈው ስህተታችን ተምረን የግል ሕይወታችንን እንድንመረምር፤ በተሰጠን አገልግሎት ያፈራነውን ፍሬ እንድንመለከት በቀሪው ጊዜያችን የበለጠ እንድንሰራ ከማናቸውም ጊዜ በበለጠ ተስፋ ሰንቀን የምንነሳበት ወቅት በመሆኑ ዓውደ አመቱን እንዲባርክልን፤ ፍቅር እና ሰላም እንዲሰጠን የአንድነት ጉባኤያችን አጥብቆ ይመኛል።

……..Click here to read more

የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 15 ዓመታዊ ጉባኤ በዳላስ ቴክሳስ ተከናወነ

ከነሐሴ 29-ጷግሜን 1 20017 ዓ/ም በዳላስ ቴክሳስ ሲካሄድ የነበረው 15ተኛው ጉባኤ ተጠናቀቀ።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤ/ክርስቲያን እንዲሁም ከተለያዩ ከተሞች በመጡ ቁጥራቸው ከ230 በላይ የሚሆኑ የሰንበት ት/ቤት አባላት የተሳተፉበት ይህ የ 3 ቀናት ጉባኤ በብፁዓን አባቶች እና በሊቃውንተ ቤ/ክርስቲያን ትምህርት የተሰጠበት፣ የየዞን እንቅስቃሴዎች እና የዞን ክፍፍሎች የተገመገሙበት፣ ወደፊት የሚሰሩ ዕቅዶች እና የተለያዩ አጀንዳዎች የቀረቡበት ይህ ዓመታዊ ጉባኤ የ15 ዓመት ጉዞውን የፈተሸበት ወቅት ነበር።

2 3በተለይም የሰንበት ት/ቤት አባላት ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠችላቸው የኃላፊነት መስመር መሰረት የሚጠበቅባችውን መንፈሳዊ ግዴታ እንዲወጡ በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ የምትገኝውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ መስኮች የመርዳት ስራ ተግተው እንዲወጡ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ቤተ ክርስቲያን የምትታወቅበት እና ብቸኛ ኃብቷ የሆነውን የአብነት ትምህርት ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲማሩ እንዲሁም ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ላይ ወጣቶች ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሊቃውንቱ መልእክታችውን አስተላልፈዋል። በተለይም እሁድ ጷግሜን 1 ቀን በተደረገው የግማሽ ቀን መርሀ ግብር ላይ በሀገር ቤት የሚገኙትን የአብነት ትምህርት ቤቶችን ከማጠናከር በተጨማሪ ይህንን ትምህርት በሰሜን አሜሪካ ከማስፋፋት አንጻር የማመላከቻ እና የመተግበሪያ ኃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል። የአንድነት ጉባኤውን ስራ ለማቀላጠፍና አባላት የሚኖሩባቸውን ከተሞች ቅርበት ከግምት ያስገባ የዞን መዋቅር ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን በዚህም መሰረት የዞን መዋቅሮች ከ 7 ወደ 10 ከፍ እንዲል ተደርጓል። የ 5 አመቱ እቅድ ለውይይት ቀርቦ የማጠናከሪያ ሀሳቦች ተሰንዝረውበት ጸድቋል። በማስከተልም ከቅርብ ወራት በፊት ኃይማኖታችውን አጽንተው በመገኘታችው የተነሳ ሰማዕትነት ስለተቀበሉት ኢትዮጵያውን ሰማዕታት አስመልክቶ ስብከትና ልዩ መርኃ ግብር ቀርቧል። የእለቱ መርሃ ግብር ከመጠናቀቁም በፊት ተጀምረው ባልተጠናቀቁ የልማት ስራዎች ላይ አጭር ገለጻ ከተሰጠ በኋላ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተካሂዷል። በተለይም ከጉባኤ5ው የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ድረስ በንቃት ሲከታተሉ ለነበሩ መስማት ለተሳናቸው ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም የማስተርጎም ስራውን ያለምንም መሰልቸት ሲሰሩ ለነበሩ እህቶች አባቶች ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በመጨረሻም በአባቶች ምክር እና ጸሎት የ2007 ዓ/ም 15ተኛው ዓመት መርኃ ግብር የተፈጸመ ሲሆን ለ 2008 ዓ/ም በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ዋሽንግተን ዲሲ ከቁጥር ሳንጎድል በሃይማኖት ጸንተን በምግባር ጎልምሰን ፈጣሪያችን በሰላም ያገናኘን በሚል የህብረት መዝሙር ተጠናቋል።

በኢ/ኦ/ተ/የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 15 ዓመታዊ ጉባኤ በዳላስ ቴክሳስ

ከነሐሴ 29 – ጳጉሜን 1 (Sep 4 – 6) የሚደረገው ዓመታዊ ጉባኤ አርብ ነሐሴ 29/2007 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት (5፡00 pm) በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ፀሎትና ቡራኬ ተጀምሯል።

በዕለቱም በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ አጭር ትምህርትና የቀጣዮቹን የሁለት ቀናት ጉባኤ አስመልካቶ ገለፃ ተሰጥቶ የእለቱ መርሃ ግብር ተጠኗቋል።
ቅዳሜ ነሐሴ 30 ጠዋት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ፣ መጋቤ ጥበብ በእምነት እና ካህናት እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የመጡ የሰ/ት/ቤት አባላት በተገኙበት በፀሎት ተጀምሯል።
በዚህ ዕለት “መከሩ ብዙ ስራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” በሚል ኃይለ ቃል በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የተጀመረው የእለቱ መርሃ ግብር የአንድነት ጉባኤውን የ2007 ዓ.ም የሥራ ሂደት የዳሰሰ ዘገባ እንዲሁም ውይይት በመጋቤ ጥበብ በእምነት ስለ አብነት ትምህርት ቤት አጀማመር ሂደት እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አማካይነት እየተሰጠ ስላለው የአብነት ትምህርት ገለፃ ተሰጥቷል።
በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ስብከተ ወንጌል እንዲሁም በመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ስለ አራቱ ጉባኤያት ሰፊ ትምህርት እና ሌሎችም የተለያዩ ዝግጅቶች ቀርበው የቅዳሜ መርሃ ግብር ከምሽቱ 4፡00 ስአት (10፡00 pm) በፀሎት ተጠናቋል።