ADDRESS

2216 Goldsmith Lane
Louisville, KY 40218

PHONE

502-749-8200

ምስክርነት

በዚህ ዓምድ ስር በደብራችን በሚሰጠው የፀበል አገልግሎት ተገልገለው በእግዚአብሔር የማዳን ኃይል የተፈወሱ ምዕረመናንን የምስክርነት ቃል ይቀርባል።

ብቻውን ኃይልን የሚያደርግ የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር  ስሙ የተመሰገነ ይሁን ! አሜን ፤

ስምና አድራሻቸውን በምስክርነት መስጫ ቅጽ ላይ ሞልተው ነገር ግን ስምና አድራሻዬ ሳይገለጽ በቤተክርስቲያኑ የህትመት ውጤቶች ወይም በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ላይ ይህ ምስክርነት ቢገለጽ አልቃወምም ያሉ ተገልጋይ ምዕመን   የታደረገላቸውን ድንቅ ሥራ እንደዚህ መስክረዋል። መልካም ንባብ !

+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

ድንቅ ተዓምር

+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

—————————————————————————————————————————————————————————————————

በሴንት ሊውስ ሚዙሪ ነዋሪዎቹ አቶ ግሩም ስዩምና ባለቤቱ ወ/ሮ ትዕግስት ተስፋዬ የደስታ አንባ እያነቡ የተደረገላቸውን ድንቅ ነገር እንደዚህ ይመሰክራሉ። ህፃን ልጃችን ቤታኒ ስዩም በሲዠር /የሚጥል በሽታ/ (Seizure Disorder)  ስትሰቃይ ትኖር ነበር ። ታማሚዋን እርሷን ቀድመን ታመምን ፣ተሰቃየን ማለት የማይገባ ቢሆን እርሷን አስቀደምናት እንጁ ከእርሷ ጋር እኛም አብረን እንታመም አብረን እንሰቃይ ነበር። ወላድ ምን እንደምንል ይገባዋል ። የወለደ መች ለራሱ ደስታ ይኖራል ? ልጆቹ ሲደስቱ ተደስቶ ፣ በልተው  ሲጠግቡ ወይም  ጠጥተው ሲረኩ በጥጋባቸው ተደስቶ እርካታቸውን ረክቶ ፣ሲከፋቸው ተከፍቶ ህመማቸውን ታሞ፣ የእነርሱ ስሜት እየገዛው እንደሚኖር ወላድ ብቻ ሳይሆን ከሰው የተወለደ  ሁሉ ባይወልድም ወላጆች አሉትና ስሜታችን ይረዳል።

ህመሙ ቤታኒን  በቀን ከሃያ እስከ ሠላሳ ጊዜ እየጣለ ያሰቃያት ነበር። እርሷ ይህንን ያህል በድግግሞሽ እየወደቀች ስትሰቃይ እኛም አብረን ታመን አብረን እንሰቃይ ነበር። ለቀቅ አድርጓት ስትጫወት ወዲያው ጥሎ  ደስታዋን ሲቀማት፣ ጫወታዋን ሲያቋርጥ እኛም የጀመርነውን አቋርጠን ስቃይዋን እንጋራ ነበር። ህመሙን በህክምና  ለማሸነፍ በርካታ የህክምና ተቋማትን የረገጥን፣ ከብዙ የዘርፉ ባለሞያዎች የመከርን፣ ህመም ያስታግሳሉ ወይም ይፈውሳሉ የተባሉ መድኃኒቶችን እንድትወስድ ያደረግናት ቢሆንም ህመምና ስቃይዋ ሲጨምር እንጅ ሲቃንስ ባለማየታችን ችግራችን ሁሉንም ማድረግ ለሚቻለው ልዑል አምላክ መስጠት እንዳለብን መክረን ወሰንን። በዚህ መሰረት ቤታኒ ከእናቷ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ሄዳ ፀበል እንድትፀበል ተስማምተን የአይሮፕላን ትኬት ገዝተን ለጉዞ ዝግጅት እያደረግን እያለ እዚሁ አሜሪካ ሉወቭል ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የፀበል አገልግሎት እንዳለ ሰማን ። የሰማነውን የምስራች ለማመን በመቸገራችን ደውለን ጠየቅን። የሰማነው ዜና እውነት መሆኑን አረጋርግጠው ከነገሩን በኋላ በፈለግነው ጊዜ መምጣትና መገልገል እንደምንችል ስለነገሩን በረራው የቀረው ጥቂት ቀናት ስለነበር ከጊዜው ጋር ተሽቀዳድመን ለመገልገል ወሰንን።

ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የቆየነው አንድ ሱባኤ/ ሰባት ቀን/ ነው። ዕለት ዕለት ለውጥ እናይባት ነበር። የመውደቁ መጠን በየቀኑ እየቀነሰ በመሄዱ እርሷ እንደልጅ መጫወት እኛም እፎይ ማለት ቻልን። ነገር ግን መውደቁ ፈጽሞ  ሳያቆም የበረራው ቀን በመድረሱ ወደ ሴንት ሊውስ ለመመለስ ተገደድን። ይዘን የመጣነውን ፀበል እያጠጣን ፥ በእርሱ እያባበስን መፀለያችንን ግን አላቋረጥንም ነበር። ከቀናት በኋላ  አምላከ ቅዱስ ገብርኤል ድንቅ ነገር አሳየን፤ ቤታኒ ሳትወድቅ ዋለች ። አላመንም ለሰው ማውራት ፈራን፣ በማግስቱም በሰላም ውላ አደረች ። ይህ በሰላም ውሎ ማደር ለቀናት በመቀጠሉ ዶክተሯ የሚለንን ለመስራት ቀጠሮ አሲዘን አስመረመርናት ዶክተሩ በመገረም የቤታኒን ከሲዘር ነፃ መሆን  አረጋገጠልን፤ ተቃቅፈን የደስታ እንባ አነባን። የማይሳነው አምላክ ይህን ድንቅ ነገር አድርጎ ደስ አሰኘን ። ለፀበል ታስቦ የታቆረጠው የአይሮፕላን ትኬት ለዘመድ ጥየቃ ዋለ። እግዚአብሔር  ስሙ የከበረ የተመሰገነ ይሁን ! ብለዋል።

—————————————————————————————————————————————————————————————————

“  . . .ልጄ ሳራ ከተወለደች ጀምሮ ሽንቷን የመቆጣጠር ችግር ነበረባት። ዕድሜዋ ከፍ ሲል ዳይፐር መጠቀም  ባለማቆሟ ችግሩ የጤንነት ችግር ሊሆን እንደሚችል በመገመት የህክምና ተቋማትን ደጅ ማንኳኳት ጀመርኩ። የምፈልገውን ፈውስ ባለማግኘቴ በችግር እየተገፋሁ ወይም ከአንዱ የህክምና ተቋም ወደ ሌላው እንድሄድ እየተመከርኩ  በርካታ የህክምና ተቋማትን ጐበኘሁ፥ የበርካታ የህክምና ባለሞያዎችንም ፊት አየሁ፣ ተጠየቅሁ፣ መልስ ሰጠሁ፣ ብዙ ጊዜ ተስፋና መድኃኒት እየተቀበልኩም ወደ ቤቴ ተመለስኩ፤ ነገር ግን የልጄን ጤንነት አስተካክሎ እፎይ የሚያሰኘኝ መድኃኒት ማግኘት አልቻልኩም።ሽንቷን እንድትቆጣጠር የተደረገው ጥረት ሁሉ ባለመሳካቱ ሳንወድ በግድ ከችግሩ ጋር አብረን ለመኖር ተገደድን። በዚህ ምክንያት እስከ አስራ ሶስት አመትዋ ድረስ ዳይፐር እያደረገች ቆየች።

እያደገች ስትሄድ ከእድሜ  እኩያዎቿ ተለይታ ለምን የዚህ ችግር ሰለባ እንደሆነች? ይህ ችግር መቸና እንዴት እንደሚፈታ ሁነኛ መፍትሄ ባለመገኘቱ ሕይወቴን በሙሉ ከዚህ ችግር ጋር ነው ወይ አብሬ  የምኖረው? . . . . የሚሉ ጥያቄዎች በህሊናዋ ውስጥ እየተመላለሱ እረፍት ይነሷት ጀመር ። በዚህ የተነሳ ደስተኛ አልነበረችም፤ እንደ ጐደኞቿ ስለማትጫዎት፣ ከእኩዮቿ ተለይታ ትተክዝ ስለነበር እኔም በጣም አዝን ነበር። በ2016 Summer YouTube ላይ ስለ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንና ስለፀበል አገልግሎቱ post የተደረገውን መልዕክት አይቼ የሰባት ቀን እረፍት ወስጄ ይዣት መጣሁ። ለቅዱስ ገብርኤልም  ተሳልኩ። የመጀመሪያውን ጥምቀት የተጠመቀች ዕለት ማታ ሳትሸና አደረች፤ በማግስቱ ዳይፐርዋን አውልቃ ጣለች። እነሆ አንድ አመት አለፈ፤ መፍትሄ ያጣሁለት የልጄ የጤና ችግር በቅዱስ ገብርኤል ምልጃ ተወግዶ እርሷም እንደ እድሜ እኩዩቿ መሆን ቻለች። እኔም ሀዘኔ ተወግዶ እንባየ ታብሶ በደስታ እንኖራለን።  ስለድንቅ ቸርነቱ እግዚአብሔር ይመስገን።  . . .” ብለውናል።

——————————————————————————————————————————————————————————————————

እህተ ማርያም ከላስቬጋስ

ሶስት ወር በሙሉ በሕመም ስሰቃይ ቆይቼ ሥራ ሳልሰራ በአልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ሕመሜም ወገቤ ላይ ስለነበር ለአምስት ደቂቃ መቆምም ሆነ መቀመጥ አልችልም ነበር፡፡በሐኪም ዘንድ ብመረመርም መድኃኒት ሊያገኙልኝ ስላልቻሉ በስተመጨረሻ በወገብሽ ላይ ያለውን ነርቭ በኤሌክትሪክ ብናቃጥለው ያሻልሻል፡ያም ሆኖ የመዳን ዕድልሽ 50% ሲሆን ይህውም የሚሆነው ከሁለት ዓመት በኋላ ነው ተባልኩ፡፡እኔም ወገቤም ተቃጥሎ፡የመዳን እድሌም አነስተኛ ከሆነ ቢቀር ይሻላል በማለት ሁሉን ነገር ትቼ ገንዘቤንም ጨርሼ በአልጋ ላይ ተኝቼ ቀረሁ፡፡የህመሜን ነገር የምታውቅ በኢንዲያና ያለች ጓደኛዬ የቅዱስ ገብርኤል ጸበል በሉውቭል ኬንታኪ መኖሩን እና እንደሚፈውሰኝም ነገረችኝ፡፡እኔም በሕመሜ ምክንያት ሥራ ስላልነበረኝ የመጓጓዣ ትኬት የሚቆርጥልኝ ዘመድ ፈልጌ በዕለተ ሐሙስ (7/11/13) ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ገበሁ፡ጸበሉን መከታተል ጀመርኩ፡በእግዚአብሔር ቸርነት እና ባጠመቁኝ ካህን (መላከ ኃይል ቀሲስ ፍቅረየሱስ) ጸሎት በስድስተኛው ቀን ሲፈታተነኝ የነበረው በሽታ ከሰውነቴ ላይ ተነሳ፡ እኔም የረዳኝን እግዚአብሔር እያመሰገንኩ በቆየሁባቸው ቀናት የደብሩ ምእመናን ስላደረጉልኝን ነገር ሁሉ ምስጋና እያቀረብኩ ወደ ነበርኩበት ሀገር (ላስቬጋስ) ተመለስኩ፡፡

ይህንን ላደረገ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ምስጋና አቀርብለት ይሆን!