ADDRESS

2216 Goldsmith Lane
Louisville, KY 40218

PHONE

502-749-8200

የቤተ/ክርስቲያናችን መልእክት / Our Church Message

እንግዶችን መቀበል አትርሱ (ዕብ 13 1)

በሊቀ ካህናት አያልነህ አርአያ፤

 

ይህ ምክረ ቃል የታላቁ ሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ነው።በዚህ ቁጥር  የተፃፈውን ሙሉ ዐረፍተ ነገር ስናነብ ሁለት ቁም ነገሮች እንደ ተሰናስሉበት እንመለከታለን።  የመጀመሪያው ሃሳብ እንግዶችን መቀበል እንዳለብን እና ይህንንም በታላቅ መንፈሳዊ ትጋት መፈጸም እንደሚገባን የሚመክር  ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ  ለምን የሚል ሞጋች ህሊና ቢኖረን እንኳ የመትጋታችን  ምክንያት ወይም ታሳቢው ውጤት ምን እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ለማስረጃም ቀደምት አባቶቻችን  በዚህ ግብር ቢፀኑ የሰማይ መላዕክትን መቀበላቸውን አጣቅሶ ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረደው ሎጥ ቅዱሳን መላእክትን(  ዘፍ 19÷1- ፍጻሜ )  ፣ አብርሃም ቅድስት ሥላሴን ( ዘፍ 18፥1 )፣ ጋለሞታይቱ  ረዓብም እስራኤላዊያኑን ሰላዮች( ኢያ 2፥1- ፍፃሜ )እንግድነት ተቀብለዋል። እንግዳ መቀበል ምንም እንኳ ከተቀባዩ ለእንግዳው ብቻ  የሚሰጥ አገልግሎት ወይም  የአንድ ወገን ጥቅም  የሚጠበቅበት ሥራ ቢመስልም ከላይ የሕይወት ተመክሮዎቻቸውን  እንድንማርበት መጽሐፍ ቅዱስ የዘከረላቸው ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች  ልምድ  የሚነግረን ግን እንግዳ ተቀባዮቹ  ከእንግዶቹ የላቀ በረከትን  እንደተቀበሉ ነው። እራሱ ጌታችን  የመምጣቱን እና የዓለም ፍፃሜን ምስጢር በተናገረበት ትምህርቱ  ” እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን  መንግስት ውረሱ።  ” (ማቲ 25፥35-36) የሚለውን የጻድቃንን የፍርድ ድምጽ ለመስማት ከሚያበቁ ተግባራት አንዱ እንግዳ መቀበል እንደሆነ ”እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና ” በማለት አስረግጦ ተናግሯል ።የዚህ ምክረ ቃል ዓላማም ይህንን የተቀደሰ ሥራ በመስራት የዚህ ፀጋ ተካፋዮች እንድንሆን  ማድረግ ነው።

ይህን  መንፈሳዊ ግብር አባቶቻችን አብዝተው በመፈፀማቸው ሀገራችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊን እንግዳ ተቀባዮች መሆናችን  ሲነገር ይኖራል። “በእንተ ስማ ለማርያም ” ከሚል የአብነት ተማሪ ፣” የመሸብኝ መንገደኛ ” እሰከሚል  እንግዳ
ምግብና ማረፊያ ምንጭ ማኀበረሰቡ እንደነበረ  ሁላችንም እንረዳለን። ከሁለት ሺ ዘመናት በላይ የዘለቀው የአብነት ትምህርት አማራጭ የሥራ ማስኴጃ የበጀት ምንጭ አልነበረውም ። መምህራኑ የተቀበሉትን የማስተማር ሃላፊነት ሲወጡ ሕዝቡም የተማሪው የእለት ጉርስ በማሸነፉ ነበር ረጅሙን ዘመን የተሻገርነው። መንገደኛን ተቀብሎ እግር አጥቦ ፣ መኝታ ለቆ ፣ አብልቶ ፣ አጠጥቶ ፣ስንቅ አሲዞ ፣ መሸኘት ከተራ ሰባዊ ባህሪ የመነጨ ሰባዊ ምግባር ብቻ ሳይሆን በዚህ ትምህርት ላይ የተመሰረተና ይህንኑ በረከት አብዝቶ በመሻት የሚሰራ ክርስቲያናዊ ግብር ነበር።

የተወደዳችሁ ልጆቼ !

እዚህ የምንንኖርበት ሀገር ሆኖ ይህን በጎ ተግባር ከውኖ የዚህ በረከት ተካፋይ መሆን ግን ቀላል አይደለም። ከባድ የሚሆነው ደግሞ እንግዳ ለመቀበል የማረፊያ ስፍራ ወይም የሚበላ የሚጠጣው ነገር  በመታጣቱ ሳይሆን  በራሱ የዚህ በረከት ምንጭ የሆነው እንግዳ በቀላሉ ባለመገኘቱ ላይ ነው።ሰፊ የመኖሪያ ቤት ኖሮን ፤ የሚበላ የሚጠጣው ባልተቸገርንበት ሁኔታ ሰው አግኝቶ ደስታ መጋራት ግን ቀላል አይደለም ። በዚህ ምክንያት ከዚህ በገጎ  ግብር ርቀን የበረከቱ የበይ ተመልካች ሆነን ኖረናል።ዛሬ ግን እግዚአብሔር ይህንኑ በጎ ሥራ ሰርተን ከበረከቱ እንድንሳተፍ እዚህ ያለንበት ድረስ አምጥቶልናል። እንዲያውም አንድ ጊዜ በምናደርገው ስጦታ ዕለት ዕለት እንግዳ እየተቀበልን በማያቋርጥ በረከት ውስጥ የሚያኖረንን የዕድል በር ከፍቶልናል። “ በአንድ ድንጋይ. . . . .” እንደሚባለው ለዚህ የጥሪ ድምጽ ተገቢ ምላሽ ብንሰጥ ድርብርብ ውጤቶችን እናስመዘግባለን።

ከተራራ የገዘፈውን የቤተ ክርስቲያናችንን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ኃላፊነት “ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ “ እንዲሉ አበው በተባበረ ክንድ ብንገፋው ችግሩ ሊወድቅ ዓላማችን ደግሞ ፀንቶ ሊተከል ይችላል ።ጋን በጠጠር እንዲደገፍ የሁላችን ትንንሽ አስተዋፆ የደብሩን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ከባድ ኃላፊነት ያቀለዋል ።  ከችግሩ ጋር የሚኖረንን ቆይታም ያሳጥራል፤ “ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር “ የሚለውን ብሂለ አበው ከመጥቀስ አልፈን መቅመስ እንጀምራለን።  እንግዳ በማሳረፍ የሚያስገኘውን በረከትም እንሳተፋለን።

እንደሚታወቀው ከጥቂት ዓመታት በፊት ህሙማን ፀበል የሚፀበሉበት  የተቸገሩ ወገኖች ሳባኤ የሚይዙበት ቦታ እዚህ የምንኖርበት ሀገር አልነበረም ። ይህንን አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎች  ምርጫቸው ሁለት ነበር። አንደኛው ሀገር ቤት ሄዶ አገልግሎቱን ማግኘት ሲሆን በአቅም እጦት ምክንያት መሔድ ያልቻሉ ወገኖች ዕጣ ፈንታ ደግም አየተመኙ ከችግሮቻቸው ጋር ተስማምቶ መኖር ነበር ። እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ እዚሁ መፍትሔ ሽቶ ህዝቡን ማገልገል ከጀመረ ዓመታት ተቆጠሩ።በአጥቢያችን የተጀመረውን ይህንን የፀበል አገልግሎት በርካቶች ከተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች ፣ ከአውሮፓና ከካናዳ ጭምር እየመጡ ተጠቅመውበታል። ህሙማን ተፈውሰው፣ እያነቡ የመጡ እንባቸው ታብሶ በደስታ ፣ ከጥያቄ ጋር የመጡ መፍትሔ አግኝተው በምስጋና ወደመጡበት ተመልሰዋል።ዛሬም በርካቶች ዕለት ዕለት እየመጡ እየተገለገሉ ይገኛሉ።እግዚአብሔር የማዳን እጁ የማያጥር ፤ልስጥ ብሎ የማያልቅበት በመሆኑ የእርሱ የማዳን ፀጋ በዝቶ፣ ስጦታውም ተትረፍርፎ  እያለ ሰው ሰራሹ አቅም አጥሮብን እየተቸገርን እንገኛለን።
ቤተ ክርስቲያኑ ሰፊ ይዞታ፣ እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት አንግዶች ሊያሳርፉ የሚችሉ ስምንት የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ፣ ስምንት የመጸዳጃ ቤቶችና አራት ሻወር፣ ምግብ ማብሰያ ኪችን እና የተዘጋጁ ምግቦች ማስቀመጫ ፍሪጆች ስለነበሩት አገልግሎቱ ሲጀመር ይመጣ የነበረውን እንግዳ ማሳረፍ የተቻለ ቢሆንም በዚህ የመቀበል አቅም ዛሬ ያለውን የመገልገል ፍላጎት ማስተናገድ የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል። ዛሬ በየቀኑ ከአርባ እስከ ሃምሳ እንግዶች ይኖሩናል። ከነዚህ መካከል ከፊሎቹ ልዩ እንክብካቤ የሚሹ እመጫቶች ፣ህፃናት፣ አና በህመም እጅግ የተጎዱ ይሆናሉ። ለነዚህ ወገኖች የተሻለ ምቾት ያለው ማረፊያ ማዘጋጀት የሚገባ ቢሆንም ይህን መመኘት እንጂ ማድረግ እጅግ ከባድ ሆኗል። የማረፊ ፣ የመታጠቢያ  እና የመጸዳጃ ክፍሎቹን በሬሾ ከላይ ለገለጽነው የሰው ቁጥር ማስላት ብቻ የችግሩን ከባድነት ከንግግር በላይ ይገልፃል። የምዕመናኑን የመገልገል ፍላጎት ላለመገደብ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና የህፃናት የመማረያ ክፍሎች በማስለቀቅ ፣ደጀ ሰላም እና ኮሪደር ላይ ጭምር በማንጠፍ እያስተናገድን እንገኛለን ።ነገር ግን የሁኔታዎቹን አለመመቸት እያወቀም ጭምር በገጠመው ችግር እየተገፋ ፈውስ ሽቶ የሚመጣው ሰው ቁጥር ግን ዕለት እለት እየጨመረ ይገኛል።

የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደርና ካህናት የአገልግሎቱ መስፋት ቢያስደስታቸውም እንግዶች እየተስተናገዱ ያሉበት ሁኔታ፣ የሚመጣው ሰው ቁጥር ዕለት ዕለት እየጨመረ መሄድ እና ይህንን የመገልገል ፍላጎት መጨመር ታሳቢ አድርጎ ለአሁን እና ለመጭው ጊዜ የሚሆን መፍትሔ አለመሻቱ ሲያሳስባቸው ቆይቷል። መፍትሔው  አሁን እየመጣ ያለውንም ሆነ ነገ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን እንግዳ  ማሳረፍ የሚችል  የእንግዶች ማረፊያ  ህንፃ መገንባት ብቻ እንደሆነ ቢታመንም  በአጥቢየው ያሉ ምዕመናን ቁጥር እጅግ ጥቂት በመሆኑ ከእነርሱ የሚገኘው አስተዋጾ የቤተክርስቲያኑን ህንፃ ሞርጌጅ ክፍያ፣ የዩቲሊቲ ወጭዎች፣ የካህናትን ደሞዝና ሥራ ማስኬጃ ሸፍኖ ሌላ ትልቅ ወጭ የሚጠይቅ ህንፃ ሊገነባ የማይችል በመሆኑ ከችግሩ ጋር ተቻችሎ መቆየት የግድ ሆኖብን ቆይቷል ።

የችግሩ ዕለት ዕለት እያደገ መሄድ ከመወሰን  እና አቅምን አስተባብሮ ችግሩን ከመጋፈጥ ሌላ ምርጫ እንደሌለ እያሳዬ በመምጣቱ  ማረፊያ የመገንባቱን ሐሣብ  አጽድቆ ወደ ተግባራዊ እንወቅስቃሴ መግባት የግድ ሆኗል። ይህን ግዙፍ ኃላፊነት ሰንወስድ አንድም እንደ  ነህምያ የሥራው ባለቤት ” የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል ፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን ፤ ” ብለን(ነህምያ 2 ፥20 )እግዚአብሔርን በማመን  ሲሆን ፤ በሌላም በኩል ደግሞ ቤተክርስቲያኑ እንደ አጥቢያ የአካባቢው ምዕመን ይሁን እንጅ  እንደ ቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮም ሆነ እንደ ተጨባጩ እውነታ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመን የሚገለገልበት በመሆኑ ከደብሩ ምዕመናን በተጨማሪ በሰሜንአሜሪካ የሚኖረውን ኦርቶዶክሳዊ አቅም በመተማመን ጭምር ነው። የደብሩን አስተዳደር እና የአጥቢያው ምዕመናን በእጅጉ እያስጨነቀ ያለው ችግር ተቃሎ የእንግዶች ማረፊያ ህንፃ ግንባታ ቢሣካ ተጠቃሚው ከከተማው  ውጭ የሚመጣው  ምዕመን በመሆኑ  ይህን ሰፊ አቅም የራሱን ማረፊያ እንዲሰራ ለማስተባበር ማሰባችን በነፍስም በሥጋ የምትጠቀሙበት በመሆኑ ነው።

የተወደዳችሁ ምዕመናን !

ይህን ችግር በአጥቢያው ምዕመናን አቅም  ማሸነፍ እጅግ ከባድ ቢሆንም በመላው ዩናይትድ እስቴት ከሚገኙ  ኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን የጥቂቶቹን እርዳታ ብቻ እንኳ ብናገኝ ግን ካሰብነው የላቀ ተአምር  መስራት እንችላለን።  በመግቢያው እንደገለጽነው ማንም ለዚህ ቅዱስ ዓላማ ስኬት ቢተባበር  ድርብርብ ውጤቶችን ያገኛል ።

ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹን ፦

  • የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደርና የአጥቢያውን ምዕመናን ችግር ተጋርቶ ችግሩን  በመፍታት የሚገኝ የመንፈስ እርካታ፣
  • የህንፃው ግንባታ የሚፈልገውን ወጭ አንድ ግዜ በመጋራት ህፃውን ብንገነባ ህንፃው ዕለት ዕለት በሚስተናግዳቸው እንግዶች ምክንያት የማያቋርጥ  በረከት ማግኘት፣
  • በቤተ ክርስቲያኑ የመቀበል ከቅም እና በተገልጋዮቹ የመገልገል ፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የወደቀውን አገልግሎት አስፋፍቶ ማስቀጠል፤
  • ህንፃውን የምንገነባው ወደ ቦታው ለፀሎት፣ ለፀበል ወይም ለሱባዔ ለሚመጡ ምዕመናን ማረፊያ በመሆኑ ወገኖቻችን በመርዳታችን የሚፈጠር እርካታ፣
  • ለራስ  ለሀገር እና ለወገን ኩራት በሚሆን  በዚህ ታላቅ ቅርስ ላያ አሻራን በማሳረፍ የሚገኝ ደስታ ጥቂቶቹ ናቸው።

ስለዚህ ከሰማይ የሚወርዱ የዝናብ ጠብታዎች ህብረት  ትልልቅ መርከቦችን የመሸከም አቅም እንደሚፈጥር እኛም ብንተባበር ከዚህ የላቀ ሥራ መስራት ስለምንችል አንድ ጠብታ ዝናብ የምታክል እርዳታ እንስጥ፣ከተባበርን  ችግሩን አሸንፈን ፣ አገልግሎቱን አስፍተን፣ በነፍስ እና በሥጋ እንጠቀማለን።  ለመርዳት ፈቃደኛ የሆነ ወገን ዕርዳታችሁን በቤተክርስቲያኑ መካነ ድር /web page/ ላይ “Donate” በሚለው ገፅ ስር ከተዘረዘሩት ሦስት የክፍያ መፈፀሚ አማራጮች በመረጠው የክፍያ ስልት መክፈል የምትችል መሆኑን እገልፃለሁ። ”

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤